በአዋሽ ተፋሰስ ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ የቅድመ-ስራ ማስጀመሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በአዋሽ ተፋሰስ ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ የቅድመ-ስራ ማስጀመሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ቢሾፍቱ ሀምሌ 9/2018ዓም (ው.ኢ.ሚ.) በአገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የጀርባ አጥንት በሆነው በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ሁለንተናዊ እቅድ ለማዘጋጀትና ለማሻሻል ያለመ የቅድመ-ስራ ማስጀመሪያ (Induction) ስልጠና መሰጠት ጀመረ።

የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር አደን አብዶ እንደገለጹት የአዋሽ ተፋሰስ እጅግ በርካታ ህዝብና መሠረተ-ልማቶች የሚገኙበት አካባቢ በመሆኑ ተፋሰሱን በዘላቂነት ለማስተዳደርና ለማልማት የሚያስችል ሁለንተናዊ እቅድ ማዘጋጀት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ትጋትና ቅንጅት ይጠይቃል ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም ይህ ስልጠና እጅግ ወሳኝ የሆኑ ሶስት ዋና ዋና ግቦች ያሉት መሆኑን በመግለጽ ከተሞክሮ መማር፣የጋራ ግንዛቤ መፍጠር፣ በቅንጅት መስራት ናቸውም ብለዋል።

በዚህም ባዮፊዚካል፣ የውሃና አየር ንብረት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ የውሃ አጠቃቀምና መሠረተ-ልማት፣ እንዲሁም ተቋማዊና ህጋዊ ማዕቀፎች መነሻ በማድረግ ሁሉንም ቡድኖች በ60/40 የተቀናጀ አሰራር ማዕቀፍ ላይ ማሰለፍ አስፈላጊ ነውም ብለዋል።

ስልጠናው የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል (WLRC) እና ከBRIGHT ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የተዘጋጀና በተፋሰሱ እቅድ ዝግጅትና ክለሳ ቡድን አባላት መካከል የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠርና ቀጣይ ስራዎችን በቅንጅት ለመምራት ያለመ መሆኑ ገልጸዋል።

ኢንጂነር አደን አብዶ ለዚህ ታላቅ መድረክ መሳካት ከፍተኛ እገዛና ድጋፍ ላደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ለWLRC ቡድን፣ ለBRIGHT ፕሮጀክት፣ እንዲሁም እውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለሚያካፍሉት አቅራቢዎች ዶ/ር ብዙነህ፣ ዶ/ር ታየ እና አቶ ጌታቸው ግዛው የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመጨረሻም የሥልጠናው ተሳታፊዎች በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በሚኖራቸው ንቁ ተሳትፎና የልምድ ልውውጥ ለአዋሽ ተፋሰስ ቀጣይ ታላላቅ ስራዎች ጠንካራ መሠረት እንደሚጥሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ ለሁለት ቀናት ለሚቆየው ስልጠና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የWLRC ቡድን እና የBRIGHT ፕሮጀክት ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በዘርፉ ሰፊ እውቀትና ልምድ ያላቸው ምሁራን ስልጠናውን በባለሙያነት በመምራት ላይ ይገኛሉ።

በስልጠነው ላይ ከኦሮሚያ ክልል ፣አፋር ክልል፣ ሶማሌ ክልል ፣አማራ ክልል እንዲሁም የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር እና የድሬ ዳዋ ከተማ አስተደደር የልማት ቢሮ ከፍተኛ ባለሞያዎች ተሳትፈዋል።

Share this Post