አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አማራጭ ሳይሆን አዋጭ ነው ተባለ።

አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አማራጭ ሳይሆን አዋጭ ነው ተባለ።

አዲስ አበባ:- ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው የፍሎራይድ ቅነሳ ፕሮጀክት (Fluoride Mitigation project) የቴክኒካል አዋጭነት (Technical Feasibility Report) በሚቀርብበት መድረክ ላይ አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አማራጭ ሳይሆን አዋጭ ነው ተባለ።

መድረኩን ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምሩ ገደፋ የፍሎራይድ ችግርን ለመቅረፍ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ በይበልጥ ችግሩ አሳሳቢና ቀስ በቀስ በጤና ላይ ችግር የሚያስከትል በመሆኑ ችግሩን ለማቃለልና ለመቀነስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአስር አመት ስትራቴጂ ዕቅድ ውስጥ በማካተት በጀት በመመደብ በዩኒቨርሲቲ ኢንዱሰትሪ ትስስር ስትራቴጂ እንዲተገበር ተደርጓል ብለዋል።

አቶ ታምሩ አክለውም እንደውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ጥራት አንዱ ቁልፍ አፈፃፀም አመላካች (KPI) በመሆኑ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የፍሎራይድን ችግር ለመቀነስ፤ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁራን የተሰራውን የዳሰሳ ጥናት ሪፓርት ምን ግኝት እንዳለና የትኛውን ቴክኖሎጂ ብንጠቀም ነው ችግሩን መቀነስ የሚቻለው የሚለውንም ታሳቢ ያደረገ መድረክ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ለቀጣይ ሶስት አመታት የሚቀጥል ሲሆን በክልል ደረጃም የፍሎራይድ ችግር አሳሳቢነት ትኩረት እያገኘ አይደለም ያሉት አቶ ታምሩ ተቋሙ ካስቀመጠው ሀገራዊ ስትራቴጂ አንፃር ከንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት እና ከውሃ ጥራት አንፃር ቢካተት የምንላቸውን ሃሳቦችን በማካተት ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት እንዲሆን ምን አይነት አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለፖሊሲ አውጪ አካል ግብዓት ለማግኘት የሚያስችል መድረክ ነው ብለዋል።

አቶ ታምሩ አያይዘውም ከፍሎራይድ ነፃ የሆነ ውሃ ለማግኘት የሚቀርበውን ዶክመንት በመገምገም ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለሚደረገው ጥረት ጥናት አቅራቢዎችን፣ ተሳታፊዎችንና አስተባባሪዎችን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አመስግነዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ኃይማኖት በለጠ በበኩላቸው በተቋሙ የፍሎራይድ ቅነሳ ፕሮጀክት ቴክኖሎጂን ዲዛይን ማድረግና አማራጮችን በመጠቀም ፍሎራይድ የሌለው የከርሰምድር ውሃ ፍለጋና ቁፋሮ ስራን ያካተተ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመውዋል።

አቶ ሀይማኖት አክለውም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚቀርበው የቴክኒካል አዋጭነት ጥናት ሪፖርት በተመረጡት ለሙከራ በተመረጡ ክልሎች ዙሪያ ጥልቅ ጥናት በማድረግ ከአለም የጤና ድርጅት /WHO/ ካወጣው ስታንዳርድ በታች የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ በቁፋሮ ከተገኘ ማጥናት አንደኛው አማራጭ ሲሆን ፍሎራይድ ያለው ውሃን በቤት ውስጥ በዘመናዊ መንገድ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በዝቅተኛ ወጪ በማከም ማህበረሰቡን ውሃ ማጠጣት ሌላኛው አማራጭ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ (Pilot Project) ሲሆን በሶስት ክልሎች ማለትም በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ዙሪያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ አካባቢ እና በኦሮሚያ ክልል ወንጂ አካባቢ የሚተገበር ሲሆን በኢትዮጰያ መንግስት በጀት ተመድቦ በቴክኖሎጂ የታገዘና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተደረገውን ጥናት ቀርቦ በጥናቱ ግኝት ላይ ውይይት ተደርጓል።

ጥናቱን ያቀረቡት ምሁራንም የቀረበው ጥናታዊ ሪፖርት በሀገሪቱ ያሉ የውሃ ሀብቶቻችን ከፍሎራይድ የፀዳ በማድረግ በማህበረሰቡ ላይ ሲፈጥር የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ተቋሙ በያዘው አቋም ላይ በዪኒቨርሲቲው ባሉ ተመራማሪዎች ችግሩን ለመቀረፍ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

በመድረኩ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከኦሮሚያና ከሲዳማ ክልል፣ ከወተር ኤይድ እና ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ጥራትና የሚመለከታቸው ባለሞያዎች ተሳትፈዋል።

Share this Post