650 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

650 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ። መስከረም 29/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር፣ በBBBC አገር በቀል በጎአድራጎት ድርጅት እና በwater net የተገነባ 650 የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ በተፈጥሯዊ መንገድ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት በአዳማ ከተማ ደንበል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል። በፕሮጀክቱ ምርቃት መርሃ-ግብር ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በተፈጥሯዊ መንገድ የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ሲያብራሩ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አካባቢን በመፍጠር የአካባቢ ብክለትን መቀነስ፣ የውሃ ጥራትን ከፍ ለማድረግና በተፈጥሯዊ መንገድ ምንም አይነት ኬሚካል ሳይጠቀሙ አትክልቶችን ለማልማት እንደሚጠቅም ገልፀዋል። ክቡር ሚኒስትር ድኤታው አክለውም አብዛኛው የህብረተሰባችን የበሽታ መንስኤ ከውሃ ብክለትና ከቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን ጋር የሚያያዝ አንደሆነ ገልፀው ይህ አገልግሎት ለመስጠት የበቃው የደንበላ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት ችግሩን ከመቅረፍ ባሻገር በትብብርና በቅንጅት የመስራትን ውጤታማነት የሚያሳይና በሀገር ደረጃ የመልማትን ተስፋ የሚያለመልም ነው ካሉ በኋላ በፕሮጀክቱ ስራ ላይ የተሳተፉትን አካለት አመስግነዋል። የፕሮጀክቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስ ታና ሜጅሬስ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ግንባታ በአጠቃላይ የባለድርሻ አካላትንና የባለሙያዎችን ስልጠና ጨምሮ 250,000.ዩሮ የፈጀ መሆኑን ገልፀው ግንባታው በ5 ወራት ውስጥ መጠናቀቁንም ጠቅሰዋል። በመጠረሻም ለስራው መሳካት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርንና waternetን አመስግነው፤ በቀጣይም ተመሳሳይ ስራዎችን በትብብር ለመስራት ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል። አቶ ኑረዲን መሐመድ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በተለይ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀው፤ ተመሣሣይ ፕሮጀክቶች ሌሎች ከተሞች ላይ ለመገንባት የታቀደ መሆኑንም አብራርተዋል። አቶ ኑረዲን አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፕሮጀክቱን የመገንባት ሂደት የውል ስምምነት ከመፈራረም ጀምሮ ሲከታተልና ሲደግፍ እንደነበረ አብራርተው የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያው በተፈጥሯዊ መንገድና በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰራ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። ከደንበላ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎች ባገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ፕሮጀክቱ ከመገንባቱ በፊት በአካባቢው ከፍተኛ የአየር ብክለት እንደነበረና በአካባቢው የሚገኘው ት/ቤት ተማሪዎች ለተለያየ በሽታ ይዳረጉ እንደነበረ ገልፀው፤ አሁን ይህ ችግር ሁሉ በመቀረፉ በጣም ደስተኞች መሆናቸውን በመግለፅ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ስሜት ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል። በፕሮጀክቱ ምርቃት መርሀ-ግብር ላይ ክቡር ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞን ጨምሮ የBBBC ሀላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የwaternet ፕሮጀክት ተወካዮችና ዶነሮች የአዳማ ከተማ የውሃ አገልግሎት ጽ/ቤት አመራሮች፣ አባገዳዋች፣ ሀደስንቄዎችና የደንበል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል። በመርሃ -ግብሩ ላይ በፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

Share this Post