በዩኤንዲፒ /UNDP/ የአፍሪካ ሚኒግሪድ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ወርክሾፕ እየተካሄደ ነው።
በዩኤንዲፒ /UNDP/ የአፍሪካ ሚኒግሪድ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ወርክሾፕ እየተካሄደ ነው። አዳማ# የካቲት 30/2018 ዓ/ም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዩኤንዲፒ /UNDP/ የአፍሪካ ሚኒግሪድ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ወርክሾፕ በድሬ ሆቴል እየተካሄደ ነው። የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጠው የባለድርሻ አካላት የታዳሽ ሚኒግሪድ ልማት የማማከርና የማስፈፀም አቅም ማሳደግ በሚል ርዕስ በዘርፉ የአለም አቀፍ አማካሪዎች መሆኑ ተገልጿል ። መርሃግብሩን በንግግር ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ኢትዮጵያ የበርካታ የታዳሽ ሀይል ምንጭ ባለቤት መሆኗን ገልፀው የተመረተው ታዳሽ ሀይል በአግባቡ ተጠራቅሞና ተቆጥቦ ጥቅም ላይ መዋል አለበት ብለዋል። ታዳሽ ሀይል አመንጪዎች አንዴ ማመንጨት ከጀመረ ማቋረጥ ስለማይቻል የሚመረተውን ሀይል በአግባቡ በማጠራቀም ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ጥበብ ፣ክህሎትና ዘዴ ስለሚያስፈልግ የባለድርሻ አካላት የአቅም ማሳደግያ ወርክሾፕ ተዘጋጅቷል ብለዋል። ክቡር ሚኒስትር ድኤታ ከፀሐይ በሚገኝ ታዳሽ ሀይል ላይ እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶ የምሰራበት ምክንያት ኢትዮጵያ በምድር ወገብ አካባቢ የምትገኝ ሀገር በመሆኗ ዓመቱን ሙሉ የፀሐይ ብርሃን የማግኘት ዕድል ስላላት በአግባቡ ተመርቶና ተጠራቅሞ ጥቅም ላይ መዋል ስላለበት ነው ብለዋል። ከፀሐይ የሚገኝ ታዳሽ ሀይል ከጊዜ ወደ ጊዜ ብቃቱ እየጨመረ ለማምረት የሚያስፈልገው ወጪ እየቀነሰ መምጣቱ ተመራጭ ያደርገዋልም ብለዋል።ዶ/ር ሱልጣን አያይዘው የሀገራችን የመሬት አቀማመጥ ወጣገባ መሆኑና ህዝቡ ተበታትኖ የመኖር ሁኔታ ሰስላለው ሁሉም ቦታ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ማዳረስ ስለማይቻል የፀሐይ ሀይልን በአግባቡ መጠቀም የግድ ይላል ብለዋል።
የፀሐይ ታዳሽ ሀይል የከርበን ልቀትን ከመቀነስ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ የግብርናን ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር፣ የገጠርንና የከተማ አኗኗርን ከማስተሳሰርና ከማሳለጥ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል። በመጨረሻም ይህን ትልቅ አቅም ያለውን የታደሽ ሀይል አመራረት፣ አጠቃቀም፣ የማጠራቀሚያ ና የማከማቻ ዘዴ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ለመተግበር የሚያስችል አቅም የሚገኝበት ወርክሾፕ በመሆኑ ተሳታፊዎች ተኩረት ሰጥተው እንዲሳተፉ የአደራ መልዕክታቸውን ዶ/ር ሱልጣን አስተላልፈዋል። በዕለቱ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ ስልጠና እየሰጡ ሲሆን ወርክሾፕ ለቀጠይ 3ቀናት እንደሚቀጥል ተገልጿል።