ኢትዮጵያ እና የታዳሽ ሀይል ዘመን፡ ወደ አፍሪካ የሀይል ማዕከልነት የሚደረግ ጉዞ
ግንቦት 10/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል (Renewable Energy) ልማት ረገድ በአፍሪካ አልፎ ተርፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እምቅ አቅም ካላቸው ሀገራት አንዷ ሆና ተጠቃሽ ስፍራ ይዛለች።
በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለችው ሀገሪቱ ከ90 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ሀይሏን ከንፁህና ለአካባቢ ተስማሚ ከሆኑ የታዳሽ ሀይል ምንጮች በማመንጨት በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ረገድ በአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ያላት መልክአ-ምድራዊ አቀማመጥና የተፈጥሮ ፀጋዎች የተለያዩ የሀይል አማራጮችን እንድትጠቀም አስችለዋታል። ከእነዚህ ውስጥ የውሃ፣ የንፋስ፣ የጂኦተርማል እና የፀሀይ ሀይል ዋና ዋና ምንጮች ናቸው።
ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ በቂ የፀሀይ ብርሃን የምታገኝ ሀገር በመሆኗ፣ በተለይም ከብሄራዊ የሀይል አውታር ውጪ ለሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች የፀሀይ ሀይል ትልቅ መፍትሄ ሆኗል።
የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማሳደግና የአፍሪካ የሀይል ማዕከል ለመሆን ኢትዮጵያ በርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ትገኛለች። ከነዚህም መካከል የታላቁ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ሀይል ፕሮጀክት ሆኗል።
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ጊዜ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትና ለቀጠናው የሀይል ንግድ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት እንደ ኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ በተመጣጣኝ ዋጋ ሀይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት ከመስራቷም በላይ የቀጠናውን ሰላም ለማረጋጋት እና ወዳጅነትን ለማጠናከር በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራች ትገኛለች።
ታዳሽ ሀይሎች ካርቦን አነስተኛ ወይም ካርቦን-አልባ ሀይል ስለሚያመነጩ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ስለሆነም ኢትዮጵያ በ2030 መካከለኛ ገቢ ያላትና የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያዘጋጀችውን ስትራቴጂ ለማሳካት የታዳሽ ሀይል ዘርፍ መሰረታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የወደፊት እድገት ከታዳሽ ሀይል ልማት ጋር በቅርብ የተሳሰረ በመሆኑ ሀገሪቱ የሀገር ውስጥ የሀይል ፍላጎትን ለማሟላት፣ የኢንዱስትሪ እድገትን ለማፋጠንና የአፍሪካ የሀይል ማዕከል ለመሆን እያደረገች ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው። ለዚህ ስኬት መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ቀዳሚውን ስፍራ ይወስዳል።
የዘርፉን ስኬት ለማስቀጠል የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የሀይል ምንጮችን ማበልጸግና ዘመናዊ መሠረተ-ልማቶችን ማስፋፋት ወሳኝ ናቸው።