የናይል ሀገራ ትብብር (Naile Basin Initative) የውሃ ጥራትን ለመለካት የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ድጋፍ አደረገ፡፡

የናይል ሀገራ ትብብር (Naile Basin Initative) የውሃ ጥራትን ለመለካት የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ድጋፍ አደረገ፡፡ መስከረም 19/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የናይል ሀገራ ትብብር ( Naile Basin Initative) ከ169 ሺ ዶላር በላይ ወጭ የተገዙ የውሃ ጥራት መለኪያ መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ድጋፍ አድርጓል፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የናይል ሀገራት ትብብር የውሃ ሀብታችን በጥራትና በመጠን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመለካት የሚያስችሉ የውሃ ጥራት መሳሪያዎችን ድጋፍ በማድረጋቸው በእጅጉ አመስግነዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ የውሃ ጥራትና መጠን ልኬት ጉዳይ በተለይም በአውሮፓ ሀገራት ውስጥ በትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ጠቅሰው ወደ ወንዝ የሚገባውም ሆነ የሚወጣው እያንዳንዱ ሊትር ውሃ ክትትል ሊደረግበት እንደሚገባና እስካሁን እንደሀገር በዚህ ደረጃ አለመሆናችንን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በሚፈለገው ልክ በጥራት በመለካት ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ግንባር ቀደም ሆና እየሰራች ነው ብለዋል። ባህላዊ ዘዴዎችን በመጠቀም የውሃ ሀብትን በጥራና በመጠን ለመለካት የምንጠቀምባቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተፋሰስ ጣቢያዎች አሉን ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ነገር ግን አንድ ቀን የናይል ትብብር ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ልክ እንደ አባይ ግድብ መረጃ የሌሎች ተፋሰሶቻችን የጥራት መረጃ በዲጅታል ኤግዚብሽን እስክሪኖች ላይ እንደምናሳያችሁ እርግጠኞች ነን ብለዋል፡፡ የኢትዮያን የውሃ ሀብት በጥራትና በመጠን ክትትል ማድረግ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ የተደረገው ድጋፍም የኢትዮጵያን ወንዞች የጥራት መረጃ ለማሰባሰብ እና ለመጠቀም ተጨማሪ መሳሪያዎችን እንድናገኝ ያነሳሳናል ብለዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ በኮሪደር ልማት እየሰሩት ያለው ስራ ከተማን ከማስዋብ ባለፈ የውሃ ሀብት ጥራት ላይ የሚያሳርፈው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በጎርፍ ምክንያት ተጠርገው ወደ ወንዞቻችን የሚገቡ ተረፈ ምርቶች ወንዞቻችን የሚበክሉበትን ሁኔታ የሚያስቀር ትልቅ ልማት በመሆኑ ሊመሰገኑ እንደሚገባና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህንን ልማት በመደገፍ ረገድ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሎረንስ ግሬስ ለኢትዮጵያ የተበረከተው የውሃ ጥራት መለኪያ መሳሪያ የናይል ተፋሰስ አገሮች ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይና የናይል ውሃ ንጹህ ፣ ዘላቂና የመጭውን ትውልድ የንሮ ደረጃ ማሻሻል የሚችል እንዲሆን ነው ብለዋል። በሚኒስተሮች ምክር ቤት የተቋቋመው የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዘላቂ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማስፈንና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ራዕይን የሰነቀ ነው ብለዋል። ራዕይዩን ለማሳካትም ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮችን በማጠናከር ዘላቂነት ያለው የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማልማት ይሰራልም ብለዋል። ለሚኒስትሪው ድጋፍ የተደረገው የውሃ ጥራት መለኪያ መሳሪያ የክትትል ስርዓቱን አቅም ለማሳደግ በእጅጉ እንደሚያግዝ እና በጋራ በመሆን የውሃ ጥራትን በተገቢው መንገድ መምራት እንደሚቻልም ነው ዶ/ር ፍሎረንስ የገለጹት። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ እየሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ፍሎረንስ ለዚህ ደግሞ ሚኒስትሩ ያላቸው ቁርጠኝነትና ስትራቴጅካዊ አመራራቸው ሊመሠገን ይገባል ብለዋል። ኢ/ር ማርክ ኦሎን በበኩላቸው ( Eng.Mark Olonde from Kenya) የውሃ ጥራት መለኪያ መሳሪያዎቹ በተገቢው መንገድ ለአገልግሎት እንዲበቁ ለላብራቶሪ ቴክንሺያኖችና ለሀይድርሎጂስት ባለሙያዎች በቀጣይቹ ሶስት ቀናት ስልጠና ይሰጣል ብለዋል። የተደረገው ድጋፍ በውሃ ጥራት ላይ ለሚሰራው ስራ ጥሩ ግብዓት መሆኑንና እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በዘርፉ ከተቀመጡ ችግሮች አንዱንና ዋናውን ይፈታልም ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማህበረሰቡን በመጠቀም መረጃ የሚሰበስብበት( citizen science) መንገድ ወጭ ቆጣቢና የውሃ ጥራትን ለመከታተል ውጤታማ ዘዴ መሆኑንም ነው ኢ/ር ማርክ የገለጹት። በእለቱ የውሃ ጥራት መለኪያ መሳሪያዎቹን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በይፋ ርክክብ አድርገዋል። በእለቱ የውሃ ጥራት ቁጥጥር እና የላብራቶሪ ተቋማት አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና አላማ በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስልም የተዘጋጀ ጽሁፍ ቀርቧል። የእለቱን መርሃ ግብር የመሩት ዶ/ር አብርሃ አዱኛ ናቸው።

Share this Post