የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከጃፓን አለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (JICA) ጋር ቀጣይ በትብብር በሚሰሯቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ።

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከጃፓን አለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (JICA) ጋር ቀጣይ በትብብር በሚሰሯቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ። አ.አ:-ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከጃፓን አለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (JICA) ጋር ቀጣይ በትብብር በሚሰሯቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ። መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ፈቃዱ በ JICA እና EWTI መካከል ያለው ትብብር እ.ኤ.አ 1998 ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከJICA ጋር የረጅምና ትርጉም ያለው ታሪክ እንዳላቸው አስታውሰው፤ የቴክኒክና ተቋማዊ ድጋፎችን በማድረግ የሰው ኃይል አቅማችንን፣ ቴክኒካል ብቃታችንን፣ የላብራቶሪ ፋሲሊቲዎችን እና ተቋማዊ ልማት ጥረቶቻችንን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል። የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ዘላቂነት ለማሻሻል ብሎም ድርጅታዊ እና አስተዳደራዊ አቅምን ለማጠናከር ያለመው ፕሮጀክት ለቀጣይ አራት አመታት በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ቀጣዩን ምዕራፍ በይፋ ይጀምራል ያሉት አቶ ታምሩ በውሃ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችንና ፍላጎቶችን ባለን ጠንካራ ግንኙነት ተቋማትን፣ አዳዲስ ቴክኒካል አካሄዶችን እና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቶችን ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል። አቶ ታምሩ አክለውም የውይይቱ ዓላማ የአፈፃፀም ዝግጅቶች እና የሚጠበቁ ውጤቶች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖርና በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ የግንኙነት መድረክ ይፈጥራልም ብለዋል። በኢትዮጵያ የJICA ተወካይ Mr. Hiroyuki Yakushi በበኩላቸው በአዲስ መልክ ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ጋር በጋራ ለመስራት ይፋ ያደረግነው ፕሮጀክት የወደፊት ትብብርን በአቅም ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ህይወት አስተማማኝ፣ ጥራት ያለውና ዘላቄታዊ ውሃ ማግኘት የኢኮኖሚ ልማት መሰረታዊ በመሆኑ በኤሌክትሮ ሜካኒካልና በቁፋሮ ቴክኖሎጂ ላይ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለውሃ ሴክተሩ ድጋፍ ለማድረግ ነው ብለዋል። Mr. Hiroyoki አክለውም ኢትዮጵያ የውሃ አቅርቦት አገልግሎትን በማስፋፋት ረገድ ጉልህ እድገት ብታስመዘግብም እነዚህን ድሎች ለማስቀጠል መሠረተ ልማትን ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተቋማትንና የሰለጠነ የሰው ሃይል ሊኖር ይገባልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአቅም ግንባታ ክንፍ ነው ያሉት በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የስልጠናና ማማከር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ጉደታ JICA የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ስልጠና እንዴት እንደሚሰጥና የስልጠና ሞጁል እንዴት እንደሚዘጋጅ ሲደግፍ እንደነበረ አብራርተው፤ ለቀጣይ አራት አመታት ደግሞ ተቋሙ ራሱን ችሎ እንዲቀጥል፣ እንዴት ገበያውን መያዝ እንደሚቻልና የደንበኞችን እርካታ ላይ የማብቃት ስራን ለመስራት መሆኑን ገልፀዋል። ከአስራ አምስት አመታት በፊት ከJICA ጋር የነበረውን ጠንካራ ግንኙነት ያስታወሱት አቶ አለማየሁ የውሃ ዘርፍ ባለሞያዎችን በማብቃት ህብረተሰቡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሲሰጡ እንደነበረም አክለዋል። በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አጃናው ፈንታው በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የውሃ ልማት ዘርፉን ፈጣንና ውጤታማ ለማድረግ ለሚያደርጉት ትብብርም የJICA ቡድንንና የውይይቱን ተሳታፊዎች አመስግነዋል።

Share this Post