በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በ HoARECN የሚተገበረው ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።
ቡታጅራ፡- ነሀሴ 25/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በ Horn of Africa Regional Environment Center and Network (HoARECN) የሚተገበረው ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዝዋይ ሻላ ሀይቅ ንዑስ ተፋሰስ ላይ የሚተገበረው ፓይለት ፕሮጀክት የደረሰበትን ደረጃ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ከህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ጋር የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ፕሮጀክቱ ውሃን ፣ መሬትንና ሰውን ማእከል አድርጎ ለአንድ ዓመት ተግባራዊ የተደረገው ፓይለት ፕሮጀክቱ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በምስቃን ወረዳ አካሙጃ ሸርሸራ ቀበሌ ተግባራዊ ሲደረግ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ፣ የውሃ ሀብት ግኝትንና ጥራትን በማሳለጥ ከተፈጥሮ ጋር በተጣጣመ መልኩ ለተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል ።
አክለውም ፕሮጀክቱ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የአካባቢ መራቆትን የምንጠብቅበት (nature based) የመፍትሔ አቅጣጫ በመሆኑ የአፈር መሸርሸርን የሚከላከሉና ተፈጥሮን በዘላቂነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች ተግባራዊ በመሆናቸው የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ ለሚሰሩ ስራዎች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የአየር ንብረትን ፣ ሴቶችንና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን አካቶ መተግበሩ ልዩ እንደሚያደርገውም ነው አቶ ደበበ የገለፁት።
በመስቃን ወረዳ የግብርና ፅ/ቤት የተፋሰስ ልማት ባለሙያ አቶ ጃቢል ሻፊ በበኩላቸው ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ሲሰራ የተጎዳው መሬት እንዴት ማገገም እንደሚችል ህብረተሰቡን በማስገንዘብ ውጤታማ ስራ ተሠርቷል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የሰው ጉልበት፣ ወጪና ጊዜ ቆጣቢ የሆነውን አዲሱን ቴክኖሎጂ ያስተዋወቅንበት ነው ያሉት ባለሙያው ተፈጥሮውን በጠበቀ መልኩና መሬቱ ሳይጎዳ፤ በአርሶ አደሩ መካከል የሚፈጠርን የድንበር ጥያቄን ሳያስነሳ አርሶ አደሩ በቀላሉ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ በአካባቢው ላይ ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያስችል በመሆኑ በቀጣይ ተሞክሮውን ወደሌላ ንዑስ ተፋሰስ የምናጋራ ይሆናል ብለዋል።
ቀድሞ ሲሰራ በነበረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይባክን የነበረውን መሬትና ጉልበት በመቆጠብ ረገድም ትልቅ አበርክቶ ያለው ነው ብለዋል።
ከዚህም ጎን ለጎን በፕሮጀክቱ ሴቶችና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች በማህበር ተደራጅተው እንደየ ዝንባሌያቸው ስልጠና ወስደው የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ በማምረት፣ በንብ ማነብ፣ በደሮ እርባታ፣ በፍራፍሬ፣ በመስኖ ልማትና በተለያዩ የእደ ጥበብ ሙያዎች በመሳተፍ ኑሯቸውን እያሻሻሉ መሆኑን ገልፀዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጥበበ ሲራክ በመስኖ ልማት የተደራጁት ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የሶላር ኃይልን በመጠቀም የነዳጅ ወጪንና የአካባቢውን የአየር ብክለትን በመቀነስ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡንና የኢኮ ሲስተሙን ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለመ ነው ያሉት አቶ ጥበበ የብክለት መጠንን፣ የአየር ንብረት ለውጥንና ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት ላይ በማተኮር ቴክኖሎጂውን ተጠቅመውና በአጭር ጊዜ ተለውጠው ለሌሎች ማሳያ የሚሆኑ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ነው የገለፁት።
በቀጣይም በፕሮጀክቱ በሶላር ሀይልና የጣሪያ ላይ የዝናብ ውሃን በማሰባሰብ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንባቸውን ፓይለት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እናደርጋለን ብለዋል።