የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች( Faecal Sludge Treatment Plant) ተገንብተው ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ጥር 28/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ ጋር በጋራ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታቸውን በጥሩ አፈጻጸም እያከናወኑ ላሉ አራት ከተሞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።
በስልጠናው መክፈቻ የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት መሪ ሰራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን ሙሃመድ በሁለተኛው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት በርካታ ሰራዎች መከናወናቸውን ገልጸው በተለይም ለሳኒቴሽን መሠረተ ልማት በተሰጠው ትኩረት በርካታ መዋለ ንዋይ ፈሶባቸው የተገነቡ ፕሮጀክቶች ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ የሚጠበቀውንና የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ ዘላቂነታውን ለማረጋገጥ የአቅም ግንባታ ስልጠናው ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዚህ ፕሮጀክት የተጀመሩትን ስራዎች በቀጣይ እያሰፋን መተግበር ይጠበቅብናል ያሉት አቶ ኑረዲን ዛሬ የተጀመሩ ሰራዎች ሲጠናቀቁ ወደ ሌሎች ከተማዎች እያሰፋን ከተማዎችን ለነዋሪዎች ምቹና ማራኪ ለማድረግ ከፍሳሽ ጋር የተያያዙ ሰራዎችን በአግባቡ ማስተዳደር ይጠበቅብናልም ብለዋል።
የዛሬው የውይይትና የስልጠና መርሃ ግብር ዋና አላማም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ዘላቂነት ከማረጋገጥ አኳያ ምን ማድረግ እንዳለብን፣ በቀጣይ እንዴት መተግበር እና ማጠናቀቅ እንዳለብን መፍትሄ ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ኃ/ሚካኤል በሁለተኛው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ባለፉት አመታት በ22 ከተሞች የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ሲሆን ጥሩ አፈጻጸም ያሳዩ ጅማ፣ አርባምንጭ ፣ሻሸመኔና ወላይታ ሶዶ ከተሞች አተገባበራቸው ምን መሆን እንዳለበት የቢዝነስ እቅድ አዘጋጅተው ወደ ተግባር ሊገቡ የሚያስችላቸውን ስልጠና ከአለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር በመተባበር ስልጠናው መሠጠቱን ነግረውናል።
እየተገነባ ያለው የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት እንደመሆኑ ከመነሻው ጀምሮ ትስስሩ ምን እንደሚመስል ፣ እንዴት እንደሚመራና የገንዘብ ወጭው በምን መልኩ መሸፈን እንዳለበት ወጭና ገቢን በግልጽ የሚያሳይ እና በዛላቂነት ማገልገል የሚችል የቢዝነስ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል ።
ፕሮጀክቱ በአለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበር ነው ያሉት ዴስክ ኃላፊዋ የተዘጋጀው የቢዝነዝ ንድፍ እቅድ ገንቢ ሀሳቦችና ማሻሻያዎች ተጨምረውበት በየከተሞቹ ሊተገበር የሚችል ያለቀለት የቢዝነስ እቅድ ለማዘጋጀት የዛሬው የስልጠና መድረክ አጋዠ ነውም ብለዋል።
በእለቱ አራቱም ከተሞች የተዘጋጁ ንድፍ የቢዝነስ እቅዶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በነገው እለትም በሌሎች ከተሞች እየተተገበረ ባለው የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት የቢዝነስ እቅድ ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።
በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዘርፉ ሀላፊዎችና ሙያተኞች ፣ የክልል የዘርፉ ሙያተኞች ፣ የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ተሳትፈዋል።