ለሶስት ክልሎች ለውሃ ተቋማት ግንባታና ጥገና አገልግሎት የሚውሉ የክሬን ማውንትድ ትራክ (Crain Mounted Truck) ድጋፍ ተደረገ፡፡
መስከረም 28/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ከKfW ልማት ባንክና ከጀርመን መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለሶስት ከክልሎች የውሃ ተቋማት እና ሳኒቴሽን ግንባታና ጥገና አግልግሎት የሚውሉ 5 የክሬን ማውንተር ትራክ (Crane Monitor Track) ማሽኖች ድጋፍ ተደረጓል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ 5ቱን የክሬን ማውንትድ ትራክ(Crain Mounted Truck) ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ካንትሪ ተወካይ ከዶ/ር አቡባካር ካምፖ (D.r Aboubacar Kampo UNICEF Ethiopia Country Representative) ተረክበዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር አንድ አካል በመሆን በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ለክልሎቹ የተደረገው ድጋፍ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ሀላፊነትንም መወጣት በመሆኑ አመስግነዋል።
የተደረገው ድጋፍ ለትግራይ ፣ አማራና አፋር ክልሎች የውሃ ተቋማትን ለመጠገን ፣ መልሶ ለማቋቋምና ሌሎች የውሃ ና ሳኒቴሽን ተቋማትን በመገንባት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ስፔሻሊስት ባሳዝን ምንዳ (ኢ/ር) በመንግስት እቅድ መሠረት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በርካታ ሰራዎችን እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ የተደረገው ድጋፍም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
ድጋፉ ከKfW እና ከጀርመን መንግስት በተገኘ ገንዘብ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ለትግራይ 1፣ ለአፋር 1፣ ለአማራ 3 በድምሩ 5 ክሬኖችን የመጠጥ ውሃ ተቋማትን ለመጠገንና መልሶ ለመገንባት የተደረገ ሲሆን ለአንድ አመት የሚሆኑ መለዋወጫዎችን ፣ የነዳጅና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ ከ1.7 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎባቸዋል ብለዋል።
ክሬኖቹ እያንዳንዳቸው ከ10 ቶን በላይ የመሸከም አቅም ያላቸው እና የመጠጥ ውሃውን የመጠገንና መልሶ የመገንባት ፕሮግራምን የሚደግፉ በመሆናቸው የጀርመን መንግስትና KfWን በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ እና በመንግስት ስም አመስግነዋል።
የአፋር ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሻሚ እንደ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ በርካታ የውሃ ተቋማት ላይ በደረሰው ጉዳት አገልግሎት የማይሰጡትን ለመጠገን ትልቅ አቅም የሚሆን ድጋፍ ተደርጎልናል ብለዋል።
ክልሉ ሞቃታማና የውሃ አጠር በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፣ ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች እና በክልሉ አቅም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊው በተለይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በከተሞች ያለውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ በብድርና በተለያዩ ድጋፎች በርካታ ከተሞቻችን ላይ ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቁ አድርጎልናል ብለዋል።
በዩኒሴፍ ድጋፍም በርካታ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
በ2017ዓ.ም ብቻ በጥገናና የማስፋፋት ስራ 100 የውሃ ተቋማትን ወደ አገልግሎት አስገብተናል ፤ የመጠጥ ውሃ ሽፋናችንም 59 በመቶ ማድረስ ችለናል የተደረገልን ድጋፍም ከዚህ በላይ እንድንሰራ በእጅጉ ያግዘናል ብለዋል።
የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ጥላሁን ሽመልስ በበኩላቸው ክልሉ ሰፊ ከመሆኑና በሰሜኑ ጦርነት በሶስቱ ዞኖች በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ ዞኖች በውሃ ተቋማት ላይ በደረሰው ጉዳት ጥገናና ግንባታ ለማድረግ የተደረገልን ድጋፍ በእጅጉ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ አመስግነዋል።
እንደ ክልል 77በመቶ ያለውን የውሃ ሽፋን የበለጠ ለማሳደግ፣ በውሃ ተቋማት በየጊዜው የሚደርሱ ጉዳቶችን እየጠገኑ ወደ ሰራ በማስገባት ሳይቆራረጥ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስተባብሮ ላደረገላቸው ትልቅ ድጋፍ በቢሮው ስም አመስግነዋል።
በተያያዘ ዜና ክቡር ሚኒስትሩ ከዴንማርክ ኢምባሲ ፣ ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ እና ከአለም ባንክ ልኡክ ጋር ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም የውሃውን ዘርፍ በማዘመን የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል መደረግ ስላለባቸውና ድጋፍ በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።