የማህበረሰብ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (CO WaSH) ፕሮጀክት የፌደራል ስትሪንግ ኮሚቴ የ2017በጀት ዓመት አፈጻጸምን በመገምገም የ2018 የበጀት ዓመት እቅድን አጸደቀ፡፡

የማህበረሰብ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (CO WaSH) ፕሮጀክት የፌደራል ስትሪንግ ኮሚቴ የ2017በጀት ዓመት አፈጻጸምን በመገምገም የ2018 የበጀት ዓመት እቅድን አጸደቀ፡፡ ጥቅምት 5/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በፊንላድ ኢምባሲ የሚመራው የማህበረሰብ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (CO WaSH) ፕሮጀክት የፌደራል ስትሪንግ ኮሚቴ በካፒታል ሆቴል ባካሄደው ውይይት የ2017በጀት ዓመት የፕሮጀክቱ አፈጻጸምን ገምግሞ የ2018 የበጀት ዓመት እቅድን አጽድቋል፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በ2017 የበጀት ዓመት ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ስምንቱ ክልሎች ጥሩ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸው የፊንላድ ኢምባሲ፣ የፌደራል መንግስት፣ ስትሪግ ኮሚቴዎቹና ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል፡፡ የስትሪንግ ኮሚቴው የውይይት ዓላማም የ2017 በጀት አመት የፕሮጀክቱን አተገባበር በመገምገም የ2018 የበጀት ዓመት እቅድን በማጽደቅ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በ 2017 በጀት ዓመት በፕሮጀክቱ ትግበራ በአንዳንድ ቦታዎች የጸጥታ ችግር ፣ የዶላር የዋጋ መዋዠቅ ፣ የግንባታ ማቴሪያል ዋጋ ንረትና መሰል ችግሮች የነበሩ ቢሆንም እነዚህን ተቋቁሞ ከፌደራል ጀምሮ እስከታችኛው የማህበረሰብ ክፍል በነበረው ቅንጅታዊ አስራር በፕሮጀክቱ ውጤታማ ስራ በመስራት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መቻሉንም ነው ክቡር አምባሳደሩ የገለጹት፡፡ የ2018በጀት ዓመት እቅድንም በሚገባ ተግባራዊ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በተሻለ መልኩ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ክቡር አምባሳደሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ በፌደራል የማህበረሰብ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (CO WaSH) ፕሮጀክት የማህበረሰብ ፕሮጀክት ትግበራ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዮሀንስ መላኩ ፕሮጀክቱ በስምንት ክልሎች በ104 ወረዳዎች ከሚያዚያ 2013ዓ.ም ጀምሮ ህብረተሰቡን በመጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን እና ሀይጅን ተጠቃሚ ለማድረግ በኢትዮጵያ እና በፊንላንድ መንግስት በሚደገፍ 45 ሚሊየን ዩሮ በሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የ2017 የበጀት አመት የፕሮጀክቱ ትግበራ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በርካታ ተግባራት የተከናወኑበት መሆኑንና ክልሎችም ሆኑ ወረዳዎች ስለፕሮጀክቱ አፈጻጸምና ዓላማ ልምዳቸውን እያዳበሩ የሄዱበትና ጥሩ ተሞክሮ የተገኘበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት የፕሮጀክቱ ትበራ ከ1 ሚሊየን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች በውሃ፣ሳኒቴሽንና ሀይጅን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ባለሙያው ለዚህ ደግሞ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ማህበረሰቡ ያለው ባለድርሻ አካል እጅና ጓንት በመሆን ችግሮችን በወቅቱ በመፍታት ለውጤታማነቱ በገንዘብ ፣ በጉልበትና በማቴሪል ያደረጉት ድጋፍ የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በ2019ዓ.ም መስከረም ላይ እንደሚጠናቀቅም ነው ባለሙያው የገለጹልን፡፡

Share this Post