ከ571 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚገነባው የአለታ ጩኮ ወረዳ የባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አፈፃፀሙ ከ80 በመቶ በላይ ነው ተባለ።

ከ571 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚገነባው የአለታ ጩኮ ወረዳ የባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አፈፃፀሙ ከ80 በመቶ በላይ ነው ተባለ።   የካቲት 19/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከሲዳማ ክልልና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት ከ571 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው የአለታ ጩኮ ወረዳ የባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አፈፃፀሙ ከ80 በመቶ በላይ ነው ተባለ።   ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ80 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት የአለታ ጩኮ ከተማ ከንቲባ አቶ ቶርባ ቶሼ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የመስክ ምልከታ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምሩ ገደፋ ፕሮጀክቱ ከውሀ ልማት ፈንድ ሪቮልቪንግ ፈንድ በብድር በተገኘ ብር የሚተገበር እንደሆነ ጠቁመው፤ ውሃ አጠር አካባቢዎች ላይ 18 ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ያሉና 4ቱ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በቀረው የአንድ ዓመት የፕሮጀክቱ ማብቂያ ቀሪዎቹን ለማጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።   በተመሳሳይ ከ23 ሺህ በላይ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ያደረገው በዳራ ወረዳ የሳፋ ቀበሌ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት የተገነባና አገልግሎት መስጠት የጀመረ መሆኑን የገለፁት የወረዳው የውሃና ማዕድን ፅ/ቤት ኃላፊና ም/አስተዳዳሪ ወ/ሮ አማረች እንዳለለት በፕሮጀክቱ የቦኖ እና የቤት ለቤት የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለመሆን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ለሰጣቸው ዕድል አመስግነዋል።   ወ/ሮ አማረች አያይዘውም ለአካባቢው ሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር አቅመ ደካሞችንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ያደረገ፣ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ራሱን የቻለና ሞዴል የመጠጥ ውሃ ተቋም መሆኑንም ገልፀዋል። የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነው የአለታ ጩኮና የዳራ ወረዳ የባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የበላይ አመራር ጀምሮ አሻራውን ያላስቀመጠ የለም ያሉት ወ/ሮ አማረች ከ24 ቀበሌዎች መካከል 7ቱ ውሃ አጠርና 3ቱ በጣም ውሃ አጠር ቀበሌዎች ተለይተውና ቅድሚያ በመስጠት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለአገልግሎት ሊበቃ ችሏል ብለዋል።

Share this Post