መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለ 440 ቤተሰብ የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ።
ጳጉሜ 05/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለ440 ቤተሰብ የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የማይቻለው ተችሎ በብዙ ውጣ ውረድና ፈተናዎች ስትፈተን የቆየችውን የኢትዮጵያችን ማንሰራራት ጅማሮ በእጅጉ ያበሰርንበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን ምርቃት ማግስት ይህንን ማዕድ ስናጋራ በእኔና በተቋሙ አመራሮች ስም የተሰማንን ደስታ እየገለፅኩ መጪው አዲስ ዓመት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመንን የምናበስርበት ነው ብለዋል።
ክቡር አምባሳደር አክለውም የዘመናት ጠላታችን የሆነውን ድህነት ወሽመጥ የተቆረጠበት ቀን በመሆኑ በዚህ ሁሉ ደስታ ውስጥ ታጅበን የምናጋራው ማዕድ በቂ ነው ብለን ሳይሆን ያለንን ተካፍለን በጋራ በዓልን ለማሳለፍ የታሰበ ነው ብለዋል።
ቀጣዩ ዘመን ትልቅ ተስፋ የምንሰንቅበት ዓመት እንዲሆን በመመኘት፤ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንዳስተላለፉም አሳስበው በዓሉ የሰላም፣ የጤናና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
በእለቱ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 አስተዳደር አቅመ ደካሞችና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ከ 4.3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ልዩ ልዩ የበዓል መዋያ ግብዓቶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሰራተኞች ለተደረገላቸው ድጋፍ በማመስገን በዓልን ሁልጊዜ አብሮነታቸውን ስለሚያሳዩን የተቋሙ የበላይ አመራሮች እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
የወረዳ 04 አቅመ ደካሞች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሚያደርግላቸው ድጋፍ በማመስገን በተደረገላቸው ድጋፍና ህዳሴ ግድባችን መጠናቀቅን አስመልክቶ ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።