ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የመረራ ሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የመረራ ሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።   ጥር 28/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመተባበር በሲዳማ ክልል በሉኮ አባያ ቀበሌ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የጸሃይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።   በምርቃት ስነ ስርአት ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በፍትኃዊነት ለሁሉም ማህብረሰብ እንዲዳረስ የመከታተልና የመተግበር ኃላፊነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ፕሮጀክትም ከሚገኙት ኮምፖነንቶች ማለትም በሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክቶች በትምህርትና እና የጤና ተቋማት የቤተሰብ የሶላር ቴክኖሎጂዎችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም ክልሎች ተጠቃሚ ማድረግ ሲሆን የሲዳማ ክልልም የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ከሚሆኑ ክልሎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።   ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በማያያዝ በመጀመርያ ዙር ከሚገነቡት 98 ሶላር ሚኒ ግሪዶች ውስጥ አምስቱ በዚህ ክልል የሚገነቡ ሲሆን ከነዚህም በመጀመሪያ ዙር ስራዎች ተጠናቀው ለምርቃት የበቃው የመሪራ ሶላር ሚኒ ግሪድ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።   ፕሮጀክቱ 632.7 ኪሎ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያለው፤ 2,500 ቤቶች ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችልና 182 ቆጣሪዎችን ተገጥመው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሶላር ሚኒ ግሪድ ነው ብለዋል። በተቋማዊ የሶላር ሲስተም/Institutional Standalone Solar System) በክልሉ የኢሌክትሪክ ተጠቃሚ ከምናደርጋቸው የ1,400 የትምህርትና የጤና ተቋማት በሲዳማ ክልል 21 የጤና ጣቢያ፣ 42 ትምህርት ቤቶች በጠቅላላ 63 የትምህርትና የጤና ተቋማት የሀይል ተጠቃሚ ይሆናሉ በማለት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።   በመጨረሻም ፕሮጀክቶቹ እንዲተገበሩ የተለያዩ ድጋፎችን ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት እና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማመስገን የኃይል ማመንጫውን ከፍተኛ ወጪ የወጣበት እና የራሳችሁ ንብረት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በባለቤትነት ስሜት እንድትጠብቁዋቸው በማለት አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወካይ እና የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ ፕሮግራም አቅርቦት ዳይሬክተር ኢ/ር ጥላሁን ብርሀኑ በክልሉ ከዋና መስመር ርቀው ለሚገኙ የህብረተሰቡ ክፍሎች የጸሀይ ሀይልን በመጠቀም የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በዚህም ከ16በላይ ፕሮጀክቶችን በተለያዩ ክልሎች ለማስመረቅ ዝግጅት እንደጨረሰ ገልጸዋል። ኢንጅነር ጥላሁን በማያያዝም በሲዳማ ክልል ሉካ አባያ ቀበሌ የተገነባውን ፕሮጀክት ስናስመርቅ የህብረተሰቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል። ኢ/ር ጥላሁን በመጨረሻም ህብረተሰቡ ባስገባው ቆጣሪ መሰረት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል።   የሲዳማ ክልል ውሀና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር ከበደ ጋኖሌ ከዋና መስመር ውጭ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የጸሀይ ሀይል በመጠቀም የሀይል ተጠቃሚ በማድረጉ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱን አመስግነው በክልሉ በመጠጥ ውሃና ላይም ውጤታማ ስራ መስራቱን ጠቁመው በሶላር ፕሮጀክትም በክልሉ አምስት ግሪድ እየሰራ ሲሆን የመሪራ ፕሮጀክትም አንዱ ነው ብለዋል።   በዚህም የጸሀይ ሀይልን በመጠቀም ህብረተሰቡን የንጹህ ኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነውም ብለዋል። ፕሮጀክቱ ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር ከ400 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ ወጪ የተገነባ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በተለዩት የገጠር እና በጣም ገጠራማ ወረዳዎች ውስጥ እስከ ሚቀጥለው አመት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውል ከገባው 147,744 ሶላር ሲስተሞችን ስርጭት ውስጥ ወደ 15,000 ሶላር ሲስተሞችን በሲዳማ ክልል ለማሰራጨት የታቀዱ እና አሁን ላይ ከ300 በላይ ሶላሮች ተሰራጭተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።   በመርሀ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣የአካባቢው ማህበረሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

Share this Post