በተቋሙ ለ 3ኛ ጊዜ የተካሄደው የረመዳን ወር የማፍጠር መርሃ ግብር የእስልምና እምነት የሚያዛቸውን ትዕዛዛት በተግባር ያሳየ መልካም ተግባር ነው ተባለ።
መጋቢት 4/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ)በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዘንድሮ ለ 3ኛ ጊዜ የተካሄደው የረመዳን ወር የማፍጠር ስነ ስርአት የእስልምና እምነት የሚያዛቸውን ትዕዛዛት በተግባር ያሳየ መልካም ተግባር ነው ሲሉ በመርሃ ግብሩ ላይ ታድመው በዱአና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች የተሳተፉት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ በሃይድሮሎጂና ተፋሰስ መረጃ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ስራአስፈጻሚ ዴስክ ሃላፊ አቶ ሙሃመድ ሷሊህ ቦሩ ተናገሩ።
አክለውም ረመዳን ወር በሙስሊሙ ዘንድ ከፍተኛ በረከት የሚገኝበት፣የቁርአንን መውረድ በማስመልከት ስግደት የሚከናወንበት በአመት ውስጥ የሚሰሩ ስህቶችና መልካም ተግባራት ውሳኔ የሚሰጥበት እንደሆነና በተለይም የደረጃ ሌሊት በምትባለው አንዲት ሌሊት የተሠራ በጎ ወይም መጥፎ ተግባር 83 ዓመ እንደተሰራ ታሳቢ ስለሚደረግ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ብለዋል።
እንዲሁም እንደ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም የማፍጠር ስነስርዓትን በጋራ ስናከብር ከምግብ ብቻ ራስን ማቀብ ሳይሆን ሁሉንም የስሜት ህዋሶች ከመጥፎ ነገር በማራቅ በወንድማማችነት እና እህትማማችነት መንፈስን በመላበስ ለተቋሙ ራዕይና ተልዕኮ መሳካት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ ለተቋሙ የሙስሊም እምነት ተከታዮች አቶ መሀመድ ሷሊህ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የማፍጠር መርሐ ግብሩን በጋራ የታደሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ፣በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ ከተቋሙ የተለያዩ የስራ ክፍሎች ስራ አስፈፃሚዎች፣ የተቋሙ ሙስሊም ማህበረሰብ እህቶችና ወንድሞች እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች ናቸው።
መርሃግብሩ መከባበርና የአብሮነት መንፈስን በማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና ስለሚጫወት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማፍጠር ስርዓቱን በማዘጋጀቱ እናመሰግናለን ሲሉም የተቋሙ ሙስሊም እህቶችና ወንድሞች ሃሳባቸውን ገልፀዋል።