የዲግ ከተማ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነች።
የካቲት 7/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአዴሌ ፕሮጀክት በሱማሌ ክልል ጀረር ዞን ዲግ ከተማ የተገነባው የሶላር ሀይል ፕሮጀክት ከተማዋን የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በዲግ ከተማ ተገኝተው የፕሮጀክቱን ስራ መጀመር አብስረዋል።
ከቡር ሚኒስትር ዴኤታው በንግግራቸው እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከዋናው የሀይል መስመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን በሶላር ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በሱማሌ ክልል ከሚገነቡ ፕሮጀክቶች አንዱ የዲግ የሶላር ሀይል ፕሮጀክት ሲሆን 350 ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚችችልና ከ2 ሺ በላይ የከተማዋን ነዋሪዎች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።
በርካታ ወጭ የተደረገበት ፕሮጀክት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ መጠበቅ፣ መንከባከብና በአግባቡ መጠቀም ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ክቡር ማኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የባዮማስ ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ናቸው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ይህም በህብረተሰቡ ጤና ላይ በተለይም ከሴቶችና ህጻናት ጤና ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር ስለሚያስከትል ይህንን ችግር የሚቀርፍና በኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ ያለው ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ነጋሽ 8,369 የከተማና የገጠር መንደሮች የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸው ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ደግሞ በሶላር ሀይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በ200 ሚሊዮን ብር የተገነባው የዲግ ከተማ የሶላር ግሪድ ፕሮጀክት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ህብረተሰቡ የመብራት ክፍያውን በአግባቡ በመክፈልና ፕሮጀክቱን በአግባቡ በመያዝ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል።
በመርሃ ግብሩ የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የዲግ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች በስፍራው ተገኝተው ደስታቸውን ገልጸዋል።