ከ219 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የማማከር ውል ስምምነት ተፈረመ።
መስከረም 07/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በ4 ክልሎች ማለትም በደቡብ ኢትዮጵያ ፣ በሶማሊ ክልል ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ እንዲሁም በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለሚያስገነባቸው 10 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ219 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከ ታርን አማካሪ፣ አዋሽ አማካሪ፤ ሚልኪ አማካሪና አሀዱ አማካሪዎች ጋር የውል ስምምነቶችን ተፈራረመ።
ስምምነቱን የተፈራረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የህብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ በተገባው የውል ስምምነት መሰረት በሚፈለገው የጥራት ደረጃና ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ባጠረ ጊዜ ስራውን እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል።
ክቡር አምባሳደሩ አያይዘውም የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የክርሰምድር ዉሀ ፕሮጀክት በአለም ባንክ ገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን ገልፀው የሚተገበርባቸው አካባቢዎች የሚኖሩት ማህበረሰቦች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩልም የተለመደው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡
ውሉን የወሰዱት አራት አማካሪ ድርጅቶች ማለትም ታርን አማካሪ፣ አዋሽ አማካሪ፤ ሚልኪ አማካሪና አሀዱ አማካሪ ድርጂት ስራ አስኪያጆች ድርጂታቸው ከዚህ በፊት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ብዙ ስራዎችን የሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ስራውን በጥራትና ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ቀድመው እንደሚያጠናቅቁ ቃል በመግባት ለስራው ቅልጥፍና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊ ዶክመንቶችን እንዲሰጣው ጠይቀዋል፡፡
የማማከር ውል ስምምነቱ በ4 ክልሎች ማለትም በደቡብ ኢትዮጵያ 3፣ በሶማሊ ክልል3 ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ 3 እንዲሁም በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ 1 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችልና በ4 ወር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡