የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸምን እየገመገመ ነው።
ነቀምቴ : ጥር 14/2017 ዓ.ም (ው.ኢ .ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የግምገማ መድረኩን በይፋ ከፍተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አፈጻጸማችን በየጊዜው በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች እየተዘዋወርን ስንገመግም ትልቅ የሆነን የውሃ ሀብት የምንመራና የምናስተዳድር እንደመሆናችን አንዳችን ከሌላችን ተሞክሮን በመውሰድ በዘርፉ የተሻለ ሰራ ለመስራት ስለሚያስችለን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የውሃ ማማ በሚል የተዛባ ትርክት ያለንን የውሃ ሀብት በአግባቡ ሳንጠቀም ቆይተናል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ አሁን ላይ የውሃ ሀብታችን እያለማን ከእኛ አልፎ ጎረቤት ሀገራትንም ተጠቃሚ ማድረግ መቻላችን እና የህዳሴ ግድባችን በተለያዩ ምሁራን ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ውሃን እያበለጸገች የተፋሰሶችን ደህንነት እየጠበቀች መሆኗን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ ባለፉት ዓመታት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አነሳሽነት 48 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውና ከ30 በመቶ በላይ ደግሞ በአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች መተከላቸው ለተፋሰሱ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረግን መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ድርቅና ጎርፍን ቀድመን ለመከላከል የትንበያ መረጃዎችን ጥራት ማሳደግም ከሰራናቸው ስራዎች አንዱ ነው ብለዋል።
በመጠጥ ውሃው ዘርፍም አመርቂ የሚባል ስራ እየተሰራ ሲሆን በተለይም ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የሚኒስትሪው አነሳሽ በሆነው የ"ግድቤን በደጀ" ፕሮጀክት በትምህርት ተቋማት ተግባራዊ በማድረግ በውሃ እጥረት ምክንያት በመማማር ማስተማር ስራው ላይ ይከሰት የነበረውን ችግር በበርካታ ትምህርት ቤቶች መቅረፍ መቻሉንም ክቡር ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በሶስቱ ዘርፎች በውሃ ሀብት አስተዳደር ፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፣ በኢነርጂ ልማት እንዲሁም በተጠሪ ተቋማታችን በአቅም ግንባታ ፣ በአየር ሁኔታ ትንበያና በህዳሴ ግድብ ተሳትፎ የተመዘገበው ውጤት በቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል በመድረኩ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅ ክቡር ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የነቀምቴ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ተመስገን እሬሳ የምስራቅ ወለጋ ዞን በእምነበረድ ፣በወርቅ ፣በቡና ምርት በቂቤ፣ በተለያዩ ባህላዊ ምግቦች እንዲሁም በተለያዩ የግብርና ምርቶች የታወቀ መሆኑን ጠቅሰው የተለያዩ የጥበብሰዎች እና የምሁራን መፍለቂያ ፣ የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት የወለጋ ሙዚየም እንዲሁም የጥንታዊቷ የማርያም ቤተክርስቲያ መገኛ ወደ ሆነችው የነቀምቴ ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ከተማዋ አሁን ላይ በተረጋጋ ሰላም ላይ እንደምትገኝና ልማቶችን እያቀላጠፈች እንደሆነ የገለጹት ም/ከንቲባው በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፣ በሳኒቴሽን ፣ በተፋሰስ ልማት አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከከተማዋ መስፋፋትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በመጠጥ ውሃ አቅርቦትና በሳኒቴሽን ላይ ያለውን ስራ አጠናክሮ ለመቀጠል የበላይ አመራሩን ትኩረት ይሻል ብለዋል።
በመድረኩ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፌደራል ፣ የክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች ፣አባ ገዳዎች ፣ሀደስንቄዎችና የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።