የ2018 በጀት ዓመት የቤዚን አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች የስድስት ወራት አፈጻጸም የግምገማ ሪፖርት ቀረበ፡፡
ጥር 16/2018 ዓ.ም./ው.ኢ.ሚ/በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ የቤዚን አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች የስድስት ወራት አፈጻጸም የግምገማ ሪፖርት ቀረበ፡፡
በዕለቱ መድረኩን የመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ናቸው፡፡
ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የሚቀርበው ሪፖርት መነሻ በማድረግ በግማሽ ዓመቱ በአፈጻጸም ደረጃቸው የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል፣በክፍተት የተለዩትን ደግሞ በቀሪ ስድስት ወራት ትኩረት ተሰጥቶባቸው የተቀናጀ የስራ መርሃ ግብር በማዘጋጀትና በመተግበር ዓመታዊ ግቡን ማሳካት ስለሚያስችል መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የአባይ ቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት፣የስምጥ ሸለቆ ሃይቆች ቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት እና የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት አፈጻጸም ሪፖርት ለተሳታፊዎቹ ቀርቧል፡፡
በተፋሰሶቹ ሪፖርት ትኩረት የተደረገባቸው ነጥቦች የዕቅድና ሪፖርት ዝግጂት፣የሰው ሃብት አስተዳደር፣የውሃ ሃብት ምደባና ፈቃድ፣የአረንጓዴ አሻራና ማህበራዊ አገልግሎት፣የውሃ ጥራት ቁጥጥር፣የበጀት አጠቃቀም፣የገጸ ምድር ውሃ ሃብት መረጃ አሰባሰብ እና የሃይድሮሎጂ ጣቢያዎችን ደረጃ ከማሳደግ አንጻር የተከናወኑ ተግባራት፣እንዲሁም ከዘርፉ ጋር በተገናኘ የሚዲያና ኮሙኒኬሸን ስራዎች አፈጻጸም ደረጃዎች ናቸው፡፡
በመድረኩ ላይ በተፋሰሶችና በጽህፈት ቤቶች ከተቀናጀ የውሃ አስተዳደር ዘርፍ ጋር በተገናኘ በሚያከናዉኗቸው ተግባራት ዙሪያ ከብሉ ዲል፣ከባዘርኔት እና ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክቶች ጋር ያላቸውን መስተጋብር በተመለከተም በጠንካራ ጎኖችና በክፍተት በተለዩ ነጥቦች ዙሪያ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው የእርስ በርስ ምላሽና ገንቢ አስተያየቶች ተሰጥተውባቸዋል፡፡
በሪፖርቱ በአብዛኛው ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው በጎ ጎኖች የተስተዋሉ ሲሆን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የተባሉት የተሟላና የተናበበ መረጃ መያዝ፣የሚዲያ ተደራሽነትን ማስፋት፣የተፋሰሱን መረጃ ማዘመን፣በተፋሰሱ የውሃ አካላት ላይ የሚደርሰውን ብክለት መለየትና ጥራቱን መቆጣጠር፣ ከፕሮጀክቶች ጋር የሚኖሩ ስራ ነክ ግንኙነቶችን ማጠናከርና ስራዎችን የጋራ ማድረግ አጽንዖት ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች፣የፕሮጀክት አስተባባሪዎች፣የቤዚን አስተዳደር ስራ አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል፡፡