የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም እየተገመገመ ነው።
ጥር 9/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ መደረኩ ላለፉት ስድስት ወራት በየዘርፉ የተከናወኑ በርካታ ጠንካራ ስራዎችን የምናስቀጥልበትና በቀጣይ ትኩረት አድርገን የምንተገብራቸውን በጋራ በመገምገም የበለጠ ውጤታማ እንድንሆን የምንችልበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ሪፖርቱ ከምን ጊዜውም በተሻለ ሁኔታ በጥራት ተዘጋጅቷል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህ ደግሞ በየዘርፉ ያሉና የስትራቴጅክ ክፍሉ ሊመሠገኑ ይገባል ብለዋል።
ኢኮኖሚያችን አሻግረን ለውጥ እናመጣለን ስንል እቅዶቻችንን በመከለስ እና ቁርጠኝነታችንን በማስቀጠል በጋራ ስንሰራ ነውም ብለዋል።
አደረጃጀትና እቅድ ማቀድ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው የሰው ሀብት ልማታችንን ሰናጠናክር በመሆኑ ላለፉት 6ወራት የዘርፉ ሪፎርም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ኢኮኖሚያችን በየጊዜው እያደገና አለም አቀፉዊ ጉዳዮች እየተቀያየሩ እንዲሁም ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ፈተናዎች በዛው ልክ እየበዙ ስለሚሄዱ ይህንን ሊቋቋም የሚችል ሲቪል ሰርቫንት ማዘጋጀት ፣ጠንካራ አደረጃጀትና ቀልጣፋ አሰራርን መዘርጋት የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ወደ ሪፎርም ተገብቷል ብለዋል።
በቀጣይም ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች የሠራተኞች አዋጅን ለአመራሩና ሰራተኞች በዝርዝር አቅርበዋል።
አዋጁ ከቅጥር ፣ ከደረጃ እድገት ፣ ብቃትና ምዘና ከደመወዝ ፣ከጥቅማጥቅም፣ ከሰራተኞች መብትና ግዴታ ፣ከስራ ላይ ደህንነት ፣ ከብዝሃነትና አካታችነት ፣ ከነጻና ገለልተኛ አኳያ በአዋጁ የተጠቀሱ ጉዳዮችን በዝርዝር አስረድተዋል።
በተጨማሪም የውሃና ኢነርጂ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ከአዋጁ ጋር ያለውን ትስስር በዝርዝር ያስረዱት አቶ ኦልቀባ ሪፎርሙ ያለ ጠንካራ የህግ ማእቀፍ መቆም እንደማይችልና አዋጁ ደግሞ የአሰራር ሂደትን፣ ተጠያቂነትን ፣ግልጸኝነትን በመደንገግ የሪፎርሙ ምሰሶዎች ጸንተው እንዲቆሙ እንደሚያደርግ በግልጽ እንደተቀመጠ አብራርተዋል።
የዘርፍ የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን የስትራቴጅክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ አለሙ መንገሻ ከውሃ ሀብት አስተዳደር ፣ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፣ ከሚቲዎሮሎጂ እና ከውሃ ቴክኖሎጂ አኳያ የተከናወኑ ዋና ጉዳዮችን እንዲሁም የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም በየአምዱ በዝግጅት ምእራፍ የተከናወኑ ተግባራትን ለውይይት በሚመች መልኩ አቅርበዋል።
በመድረኩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች እየተሳተፉ ሲሆን የቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤቾችና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት አመራሮችና ሰራተኞች ደግሞ በቨርቹዋል ሚቲግ እየተሳተፉ ነው።