የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የ2017 ዓ.ም የክረምት ስራዎችን ገመገመ፡፡
መስከረም 06/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የ2017 ዓ.ም የክረምት ስራዎች አፈጻጸም ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ በተገኙበት ተገምግሟል።
ግምገማው በአዋሽ ፣ በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች እና በኦሞ ጊቤ ወንዞች በ12ቱ ፕሮጀክቶች (12 lots) እየተተገበሩ ባሉ ስራዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኘሮጀክቱ የክትትልና ግምገማ አማካሪ በአቶ ተክሊት ብርሃነ የእያንዳንዱ የፊዝካል ስራዎች ፣ የፋይናንሻል አጠቃቀምና የግዥ ሂደቶች ያሉበት ሁኔታ ቀርበዋል።
በጽሁፉ መነሻነትም በተለይ የፊዝካል የጎርፍ መከላከል ስራውን በየፕሮጀክቶቹ (lots) የሚከታተሉ የቴክኒክ ባለሙያዎች ስራው ያለበትን አፈጻጸም አብራርተዋል። በተጨማሪም የፋይናንሻል አጠቃቀም እንዲሁም በግዥ በኩል ያለውን የአዋሽ ፣ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች እና የኦሞ ጊቤ ዘላቂ የጎርፍ መከላከል የተፋሰስ ጥናት (Basin level study) ኮንሰልታንት ግዥና የዕቃዎች የግዥ ሁኔታ ተገልጿል።
ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ መድረኩን ሲያጠቃልሉ እስካሁን ያለው አጠቃላይ አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን ቀሪ ስራዎቹን ሳምንታት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ አለባቸው ብለዋል፡፡ በየፕሮጀክቶቹ (lots) ያሉ የኮንትራክተሮች ስራ በጊዜ ተጠናቀው ርክክብ መደረግ እንዳለባቸው እንዲሁም የተጓተቱ የግዥ ሂደቶችን በማፋጠን ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበትን የፋይናንሻል አጠቃቀም ከፍ ማድረግና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙም ጭምር አሳስበዋል።
በመጨረሻም በቀጣይ ጊዜያት ጠለቅ ባለ መልኩ ግምገማ እንደሚካሄድ በማስገንዘብ ኘሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ እንደ አንድ ቡድን በመሆን መሰራት እንዳበት በማሳሰብ የእለቱ የግምገማ መድረክ ተጠናቋል።