የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የፕሮጀክት ግንባታ ለማከናወን ስምምነት ፈጸመ ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ2.8 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የፕሮጀክት ግንባታ ለማከናወን ስምምነት ፈጸመ።   ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (ው. ኢ. ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 2,887,187,046 ብር ወጪ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ፈጽሟል።   ስምምነቱን የተፈራረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የህብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ በተገባው የውል ስምምነት መሰረት በሚፈለገው የጥራት ደረጃና ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ባጠረ ጊዜ ስራውን እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል።   በስምምነቱ ወቅት እንደተገለጸው፤ ሚኒስቴሩ ከዋን ዋሽ ፕሮግራም በተገኘ ገንዘብ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን በዚህም ጥናት እና ዲዛይን፣ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ግንባታና ክትትል ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑ ተገልጿል።   በዚሁ መሰረት ከተለያዩ ተቋራጮች ጋር 12 የኮንትራት ውሎችን ፈጽሟል። የዋጪሌ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክትን ለመገንባት ከግሪን ኮንስትራክሽን ጋር የ275,696,690 ብር እንዲሁም ከዋዳ ኃላ.የተ.የግ.ማህበር ጋር 443,520,896 ብር በድምሩ 719,217,587 ብር የውል ስምምነት ተፈርሟል።   የኤልወያ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክትን ለመገንባት ደግሞ ከግሪን የውሃ ስራዎች ኮንትራክተር እና ጃርሶ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ጋር በአጠቃላይ የ949,898,163 ብር የስምምነት ፊርማ ተካሂዷል። በ1,038,218,155 ብር ወጪ የዳሮላቡ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ግንባታን ለማከናወን ከዋዳ ኃላ.የተ.የግ.ማህበር፣ ይስሃቅ አበበ ጠቅላላ ኮንትራክተር (ከጃቪስና ሽርትሊ ትሬዲንግ ኢትዮጵያን ኃላ.የተ.የግ.ማህበር በጥምረት) እንዲሁም አዲሱ የሸዋወርቅ ጠቅላላ ውሃ ስራዎች ኮንትራክተር ጋር ሚኒስቴሩ ስምምነነት አድርጓል። የኮንትራት ውል ስምምነቱ የተፈጸመው ፕሮጀክቶቹን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው።   ከእነዚህ የውል ስምምነቶች በተጨማሪ ሚኒስቴሩ የውሃ ጉድጓድ ለማስቆፈር የሚያስችል ስምምነት የፈጸመ ሲሆን፤ ከኪድመር ኢንጂነሪንግ ኃላ.የተ.የግ.ማህበር፣ ሶፍዑመር ንግድና ኮንስትራክሽን እና ፋፊ የውሃ ስራዎች ኮንትራክተር ኃላ.የተ.የግ.ማህበር ጋር በ60 ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቁ የ179,853,119 ብር ፕሮጀክቶች ውል ስምምነት ፈጽሟል።   በአጠቃላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 2,887,187,046 ብር ወጪ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ከኮንትራክተሮቹ ጋር ፈጽሟል።

Share this Post