በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኃይድሮጂን ልማትና አጠቃቀም ስትራቴጂን ወደ ተግባር ለመቀየር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መድረክ ተካሄደ።
ግንቦት 5/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጀርመን ኢነርጂ የልማት አጋር (GIZ) ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኃይድሮጂን ልማትና አጠቃቀም ስትራቴጂን ወደ ትግበራ ለማስገባት አስቻይ ሁኔታ በሚፈጥሩ ሁኔታዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር በኃይሌ ግራንድ ሞል ሆቴል መርሐ ግብር አዘጋጅቷል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጀርመን ኢነርጂ የልማት ትብብር ሃላፊ አቶ ሳምሶን ቶሎሳ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የሃይል አቅርቦትን በስፋት በመጠቀም ልማቱን ለማሳለጥ የምታደርጋቸው ጥረቶች ስኬታማ መሆናቸውን ገልጸው ተጨማሪ ታዳሽ ኢነርጂን በመጠቀም ልማቱን ማስቀጠልም ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ አተገባበሩ ላይ በሚገባ መሳተፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ሃብት ጥናት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሌብ ታደሰ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከምርት ተቋማት የሚወጣውን በካይ ጋዝ ለመቀነስ፣ ከውጭ የሚገባውን ነዳጅ በማስቀረት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማዳንና፣ ከሀገር ውጭ ግዢ የሚደረግበትን ኢአሞኒያ ማዳበሪያ በሃገር ውስጥ አምርቶ ለመጠቀም የሚያስችል ስትራቴጂ ለመቀየስ መድረኩ መዘጋጀቱን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የሚደረገው ውይይት ኢትዮጵያ በታዳሽ ኢነርጂ ያላትን ዕምቅ አቅም በመጠቀም ስትራቴጂውን ወደ መሬት በማውረድ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በመድረኩ የጀርመን የልማት ትብብር የptx (power to x)ኃላፊ ሚስ ማስቻ ኩዛይና አማካሪዋ ማሬን ስኮትለር በጋራ በመሆን ሰነድ አቅርበዋል።
በገለጻቸው በኢትዮጵያ የe-SAF(electro-sustainable aviation fuel)እና e-fertilizer (electro- fertilizer) የሚሉ አጀንዳዎች ተካተው የቀረቡ ሲሆን ታዳሽ ኢነርጂን በመጠቀም አረንጓዴ ሃይድሮጂንን ለአውሮፕላን ነዳጅ በመጠቀም ለማንቀሳቀስና ለስነ ምህዳር ተስማሚ የናይትሮጂን ማዳበሪያ በመጠቀም የምርት አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥናቶችም ተካተው ቀርበዋል።
ከቀረቡ ገለጻዎችና የጥናት ውጤቶች በመነሳት ተሳታፊዎቹ በቡድን ተከፍለው ከሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ሰፊው ጉዳዮችን በማንሳት የተወያዩ ሲሆን ከሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና አተገባበር ጋር በተገናኘ ሰፊ ጉዳዮችን በማንሳት ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ከውሃና ኢነርጂ ሚ/ር የኢነርጂ ዘርፍ ሃላፊዎችና የፕሮጀክት አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች፣ ከግብርና፣ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኃይድሮጅን ማህበር፣ የውጪና የአገር ውስጥ አማካሪዎች፣ የዩኒቨርስቲና የግል ተመራማሪዎች እና ከግሉ ዘርፍ የተሳተፉ ሲሆን መርሃ ግብሩ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም ተገልጿል ።