በትምህርትና ጤና ተቋማት ዘላቂ የኤሌክትሪፊኬሽን አቅርቦትና የክፍያ ሥርዓት ላይ ውይይት ተካሄደ።

በትምህርትና ጤና ተቋማት ዘላቂ የኤሌክትሪፊኬሽን አቅርቦትና የክፍያ ሥርዓት ላይ ውይይት ተካሄደ። ግንቦት 4/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአዴሌ ፕሮጀክት አማካኝነት በ1400 የጤናና የትምህርት ተቋማት የሚተገበረውን ዘላቂ የኤሌክትሪፊኬሽን አቅርቦትና የክፍያ ሥርዓት በሚመለከት በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ በስትሪንግ ኮሚቴ ደረጃ ውይይት አካሂዷል። የጥናቱ ዋና ዓላማ በጤናና ትምህርት ተቋማት የተገነቡ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮጀክቾች የረጅም ጊዜ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችሉ ቴክኒካልና አስተዳደራዊ አማራጮችን መለየት ሲሆን የተቋማቱ የኃይል ፍላጎት፣ የጥገና ወጪ፣ የመሣሪያ ዕድሳት እና የአስተዳደር አቅም በጥናቱ ተካትተው ቀርበዋል። ጥናቱ ከፕሮጀክቶቹ ግንባታ በኋላ ለኦፕሬሽንና ጥገና (Operation and Maintenance) የሚያስፈልጉ ወጪዎች እንዴት እንደሚሸፈኑ የፋይናንስ ሞዴሎችን በማቅረብ፣ የክፍያ ዘዴዎችን ለማሻሻል ተቋማቱ፣ መንግሥት፣ ማህበረሰብ እና አገልግሎት ሰጪዎች ሊኖራቸው የሚችለውን ድርሻ በዝርዝር አስቀምጧል። በተለይም በገጠርና ከዋናው የሀይል መስመር ውጭ (Off-grid) በሚገኙ የጤናና ትምህርት ተቋማት የኃይል አቅርቦት እንዳይቋረጥ የሚያግዙ ዘላቂ የአስተዳደርና የክፍያ ሥርዓቶችን ማቅረብ የጥናቱ ቁልፍ ትኩረት መሆኑ ተገልጿል። የፕሮጀክቱ ውጤት በጤና አገልግሎት፣ በትምህርት ጥራት እና በዲጂታል አገልግሎቶች ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለማጠናከር እንደሚያግዝም በውይይቱ ተጠቁሟል። ውይይቱን የመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ሲሆኑ፣ ላለፉት አራት ዓመታት ለኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሞች ልዩ ትኩረት በመስጠት በኃይል ዘርፍ ላይ ሪፎርም ከመካሄዱ ጀምሮ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። አክለውም ጥናቱ ከመጽደቁ በፊት የውሃና ኢነርጂ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የፋይናንስ ሚኒስቴሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በማኔጅመንት ደረጃ ከተወያዩበት በኋላ በድጋሚ በስትሪንግ ኮሚቴ እንደሚታይ ገልጸዋል። በመጨረሻም ከውይይቱ በተገኙ ግብዓቶች መነሻ ጥናቱ በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ ተጠናቆ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ፊት እንደሚጸድቅ የውሳኔ አቅጣጫ ተቀምጦ ውይይቱ ተጠናቋል።

Share this Post