አዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ፈጣን የከርሰ ምድር ውሃ ካርታ ስራ ለማጠናከር ስምምነት ተፈረመ።
ሚያዚያ 13/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከዴንማርኩ ቴም (TEM) ኩባንያ ጋር በመተባበር ፈጣን የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ካርታ ስራን ለማጠናከር የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ፈርሟል።
ስምምነቱን የፈረሙት የኢንስቲትዩቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ታመነ ሀይሉ እና የቴም (TEM) ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኔልስ ኢስቤን ናቸው።
ዶ/ር ታመነ ሀይሉ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ በአቅም ግንባታ፣ በተግባራዊ ምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በላቦራቶሪ አገልግሎትና በቴክኒካል ስልጠና ዘርፎች ላይ ተጠናክሮ እየሰራ ሲሆን፣ በየዓመቱ ከመላው አፍሪካ የሚመጡ ከ2,000 በላይ ሙያተኞችን በከርሰ ምድር ውሃ ምርመራ፣ ቁፋሮ ቴክኖሎጂ፣ ጂአይኤስ፣ የውሃ አቅርቦት ምህንድስና እና ጅኦፊዚካል ጥናቶች ላይ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር ታመነ ገለጻ ቴክኖሎጂዎች እየዘመኑ እና ችግሮች ውስብስብ እየሆኑ በመምጣታቸው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዓለም አቀፍ ልምድ ካለው የቴም (TEM) ኩባንያ ጋር መተባበር አስፈላጊ ሆኗል።
ይህ ስምምነት ለኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ የውሃ ዘርፍ ትልቅ አቅም የሚያመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ በተለይም በተራቀቁ የጅኦፊዚካል መሳሪያዎች አጠቃቀምና ጥገና ላይ ስልጠና በመስጠት፣ ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ እውቀት ለማስፋፋት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የቴም (TEM) የጥገና ማዕከል በማቋቋም ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለአጋሮች፣ ለኮንትራክተሮችና ለመንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ቴክኒካል ድጋፍ እንዲሰጥ ይጠቅማል ተብሏል።
በሌላ በኩል ዶ/ር ኔልስ ኢስቤን እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል እንዲሁም ከፍተኛ ብቃት ያለው ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት በዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ጥረቶችን ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።
እንዲሁም ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያላቸውን አጋርነት በማጠናከር ቴክኖሎጂው ውጤታማ እንዲሆን በቀጣይነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ይህ ስምምነት በአጠቃላይ ፈጣንና ትክክለኛ የከርሰ ምድር ውሃ ካርታ በመስራት፣ የሰው ኃይል አቅም በማጎልበት፣ የምርምር አቅምን በማሻሻል እና በማስረጃ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመዘጋጀት እንዲሁም የአገሪቱን የውሃ ደህንነት ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል።
በፊርማ ሰነስርዓቱ ላይ ከዴን ማርክ ኢምባሲ እና ከፕላን ኢንተርናሽናል የተወከሉ የተሳተፉ ሲሆን በኢንስቲትዩቱ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ስራዎችንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።