የመንግስት አስተዳደርና አደረጃጀት ማሳለጥ አምድ ላይ ውይይት ተደረገ።
ቢሾፍቱ፦ መጋቢት 08/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እየተሰራ ያለው የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ዘመኑ ከሚያራምደው የአስተዳደር ሳይንስ አንዱና ዋናው ቀልጣፋ አገልግሎትን ለዜጎች ማቅረብ ሲሆን የሠራተኛውን የእውቀት፣ የክህሎት፣ የአስተሳሰብ፣ የሞራል እና የባህሪ ክፍተቶች ለማስተካከል የሚሰራ ሪፎርም ነው፡፡
የተቀናጀ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ተግባራዊ ለማድረግ የዝግጅት ምዕራፍ ከሚያደርጉ ተቋማት አንዱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመሆኑ በበጀት አመቱ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባት የሚያስችል ሰነድ እየተዘጋጀ ሲሆን የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ የመንግስት አስተዳደርና አደረጃጀት ማሳለጥ አምድ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
በወይይቱ የመንግስት አስተዳደርና አደረጃጀት ማሳለጥ አምድ ላይ መዋቅር ለማዘጋጀት የሚያስችል የስራ ፍሰት፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱና የ3ቱ ተጠሪ ተቋማት የመዋቅር አደረጃጀት፣ የበፊቱን ውጤት መነሻ በማድረግ የቴክኒካል፣ የብቃትና የባህሪ ብቃት የተካተተበት የስራ መዘርዝር (Job description) እና ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ ባለሙያ ላይ እንዴትና በምን አግባብ ይሰራል ለሚለው የሙያ እድገት መሰላል (Career Structure) ሰነዶች ቀርበው በሰፊው ውይይት ተደርጎበታል፤
ውይይቱን የመሩት የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ አመዱ እንደሴክተርም ሆነ በየደረጃው ላሉ ተቋማት ከስራ ፍሰት ጀምሮ ወደ ተቋማዊ መዋቅር እና የስራ መዘርዝር ማዘጋጀትና የሙያ መሰላል ወሳኝ መሆኑን አንስተው በየቡድኑ እየተሰሩ የነበሩ በርካታ ስራዎችንም አድንቀዋል።
የሚቀሩ ሰራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚግባም ክቡር አቶ ሞቱማ አሳስበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ኦልቀባ ባሼ በበኩላቸው በ4ቱም ተቋም ትክክለኛ የስራ መደቦችን ወደ አንድ ማምጣት የሚቻል ቢሆንም ለቦታው የሚመጥንና ወጥ የሆነ የስራ መዘርዝር በማዘጋጀት ተቋሙን የሚመጠን ስራ መስራት ይገባል ብለው፤ እገዛ የሚፈለጉ ጉዳዮችን በመለየት ከሲቪል ሰርቪስም ሆነ ከአማካሪዎች ጋር በጋራ መስራት ይገባልም ብለዋል።