ልኡካን ቡደኑ በኢትዮጵያ ባካሄዱት ጉብኝት በተመለከቱት ለውጥ በእጅጉ መደመማቸውን ገለጹ፡፡

ልኡካን ቡደኑ በኢትዮጵያ ባካሄዱት ጉብኝት በተመለከቱት ለውጥ በእጅጉ መደመማቸውን ገለጹ፡፡   መጋቢት7/ 2018 ዓ.ም የዛምቤዚ የውሃ ተፋሰስ ኮሚሽን (zamcom) ከፍተኛ ልኡካን ኢትዮጵያ ከውሃ ጥበቃና ከተፋሰስ አስተዳደር ጋር በተገናኘ በምታካሂዳቸው ተግባራት ዙሪያ ልምድ ለመቅሰም ባካሄዱት ጉብኝት በእጅጉ መደመማቸውን ተናግረዋል፡፡   ጉብኝታቸውን የጀመሩት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ የተካሄዱ ለውጦችን በመመልከት ሲሆን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለይም የሪከርድና ማህደር ክፍል አሰራርን በማዘመን ረገድ ወረቀት አልባ አሰራርን በማስቀረትና የተጠያቂነት ስርዓትን ማስፈን መቻሉን አረጋግጠው ለውጦችንም አድንቀው አልፈዋል፡፡ ከውሃ መረጃ ጋር በተገናኘም ለጥናትና ምርምር አስፈላጊ የሆኑ መጻህፍትን ዲጂታላይዝ መደረጋቸውንና ለመረጃ ፈላጊዎች ዝግጁ እየተደረጉ መሆኑን ተመልክተዋል፡፡   እንዲሁም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘመነ ዲጂታል ኤግዚቢሽን ማዕከል በማቋቋሙ በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብን አሁናዊ ሁኔታ በቀጥታ ማየት መቻላቸው እንዳስገረማቸውና ይህም ትልቅ ተቋማዊ ለውጥ መሆኑን አበረታተዋል፡፡ ጎብኝዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ ከእንጦጦ እስከ አራዳ ፓርክ ባካሄዱት ምልከታም በተለይም ከወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር ተያይዞ በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸው፣ በስፍራው ትልቅ የስፖርት ስታዲየም ግንባታ መካሄዱ፣ ተጨማሪ ገቢ ሊፈጥሩ የሚችሉ ፍራፍሬና አትክልት ቦታዎች መልማታቸውና፣ የመዝናኛ ስፍራዎች ለጎብኝዎቹ ሳቢና ምቹ መሆናቸውና ሌሎች ተጨማሪ የልማት ስራዎችን መመልከታቸው አስደንቆናልም ብለዋል፡፡   በዛምቤዚ በርካታ ዛፎች እንደሚጨፈጨፉና ከመሬት ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ጋር በተገናኘ ሰፊ ክፍተት መኖሩን አውስተው ከዚህ ጉብኝት በኋላ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ዛፎችን በመትከልና የአፈር ጥበቃና የአካባቢ በማስዋብ በኩል ትልቅ ተነሳሽነት እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል። የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ጽዳትና ውበት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የተረዱት ጎብኝዎች የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደስሟ ተግባሯ እውን መሆኑንም አስመስክራለች ብለዋል፡፡   ከዚህ በመነሳት የመንግስት የግልና የህዝብ ተግባራትን ለይተን እንድናውቅና ለችግሮች መፍቻ የሚሆኑ መፍትሄዎችን ማግኘታቸውንም በልምድ ልውውጡ ተምረናል ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም እንደግብዓት ስለሚወሰድ ወደሃገሪቱ በመምጣት ተሞክሮ እንዲቀስሙ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ በአጠቃላይ ሃገሪቱ ከለውጡ መንግስት ወዲህ የሰራቻቸው ሃገራዊ ለውጦችና የመሰረተ ልማት ስራዎች ደምቀው የወጡት ሃገር ወዳድና ቁርጠኛ የሆነ መንግስት መመስረት በመቻሏ ነውም ሲሉ መስክረዋል፡፡   በጉብኝቱ የተሳተፉት የዛምቤዚ የውሃ ተፋሰስ ኮሚሽን (zamcom) ከፍተኛ ልኡካን አባላት ከአንጎላ ቦትስዋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ የተውጣጡ ሲሆኑ በነበራቸው ቆይታ ለተደረገላቸው እንክብካቤና ድጋፍ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን አመስግነዋል፡፡

Share this Post