የከርሰ ምድር ውሃ መረጃን በአግባቡ ማስተዳደር በሚል አጀንዳ የከፍተኛ ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
መጋቢት /2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብራይት ፕሮጀክት የከርሰ ምድር ውሃ መረጃን በአግባቡ ማስተዳደር በሚል አጀንዳ ከከፍተኛ ባለድርሻ አካላት ጋር በካፒታል ሆቴል የምክክር መድረክ አካሄደ፡
ዶክተር ማማሩ አያሌው የብራይት ፕሮጀክት ማናጀር በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረጉ ክንዋኔዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በርካታ ስራ እየሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡በመሆኑም በእነዚህ ተፋሰሶች ዙሪያ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ተግባራትን ለማከናወን በአባይ ፣አዋሽ፣ተከዜ፣ኦሞ ጊቤና ስምጥ ሸለቆ ሃይቆች ተፋሰሶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
አክለውም በፕሮጀክቱ ተግባራት የከርሰ ምድር ውሃ መረጃን በአግባቡ ለማስተዳደር የተፋሰስ ዕቅድ/Basin plan/የማዘጋጀት የማሻሻልና የመከለስ ስራ ስለሚከናወን ለዚሁ ግብዓት እንዲሆን በእለቱ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከዘርፉ ጋር የተገናኙ በርካታ ሰነዶች እንዲቀርቡ ለአቅራቢዎች ዕድሉን ሰጥተዋል፡፡
በዚህ መሰረት የመረጃ አያያዝ ተግዳሮቶችና ውስንነቶች፣የመረጃ ክፍተት በኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ያለው ተፅዕኖ፣የከርሰ ምድር የውሃ ጥናት ልምዶችና የመጪው ጊዜ ተግዳሮቶች፣ሃገር አቀፍ የከርሰ ምድር መረጃ ታሪካዊ ዳራና ስርዓት፣ሃገር አቀፍ የከርሰ ምድር ውሃ ግኝቶችና መሰናክሎች እንዲሁም የመረጃ ምንጮች የማግኛ ዘዴዎች በሚሉ አጀንዳዎች ዙሪያ የተዘጋጁ ሰነዶችን መነሻ አድርገው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ከብራይት ፕሮጀክት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች የተወከሉ አቅራቢዎች በስፋት ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
የሰነዱን ሃሳብ መነሻ በማድረግም ተሳታፊዎቹ አስተያየትና ጥያቄዎችን በስፋት ያነሱ ሲሆን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳና የውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌቴ ዘለቀ ምላሽ በመስጠት በተለይም የከርሰ ምድር ውሃ መረጃን በተገቢው መንገድ ማደራጀት፣መረጃዎቹ የሚገኙበትን ቦታ ማወቅ ፣ለመረጃ ፈላጊዎቹም በትክክል ማስተላለፍ እንዲቻል በአግባቡ አቅዶ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ፣ የብራይት ፕሮጀክት ዩኒት አስተባባሪ፣የክልል የውሃ ቢሮ ተወካዮች እና የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡