የጎርፍ ክስተትን በመከላከል ከተጋላጭነት ይልቅ ለዘላቂ ልማት ማዋል ይገባል ተባለ።
ሃዋሳ:- የካቲት 21/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የውይይት መድረክ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የጎርፍ ክስተትን በመከላከል ከተጋላጭነት ይልቅ ለዘላቂ ልማት ማዋል እንደሚገባ ገለፁ።
በስምጥ ሸለቆና በኦሞ ጊቤ ቤዚኖች ላይ የጎርፍ ተጋላጭነት ቅነሳ የቅድመ ጥናት ሪፖርት በቀረበበት የውይይት መድረክ ላይ ክቡር አቶ ሞቱማ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ የጎርፍ ክስተቶችን በአግባቡ በማስተዳደር የዜጎችን ደህንነት በዘላቂነት ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ ቦታዎችን በጥናት በመለየት በሰዎች ላይ ይደርስ የነበረውን የጎርፍ አደጋ ለመታደግ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ ገልፀው፤ በአዋሽ፣ በስምጥ ሸለቆ እና በኦሞ ጊቤ ቤዚን ላይ በ2.7 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚተገበር ገልፀዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ አባቡ የቅድመ ጥናቱ ዋና ዓላማ ባለፉት አመታት ከጎርፍ ጋር ተያይዞ ይደርስ የነበረውን የጎርፍ ክስተት በፕሮጀክቱ በግንባታና በዘላቂ ልማት SwS በተባለ አማካሪ ድርጅት የተሰራው ጥናት ለቤዚኖቹ ዘላቂ መፍትሔ ግብዓት በማሰባሰብ፤ ብቃትና ስታንዳርዱን የጠበቀ ዶክመንት ለማዘጋጀት ያለመ ነው ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ አክለውም ጥናቱ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከ 170ሺህ በላይ ዜጎችን ከጉዳት የሚታደግና ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ ማሳዎችን በማዳን ለ1ሺህ ዜጎች የስራ ዕድልም ፈጥሯል ያሉት አቶ ተስፋዬ የስምጥ ሸለቆና የኦሞ ጊቤ ላይ የሚሰራው ጥናት ተፋሰስ አቀፍ ሆኖ ለዘላቂ መፍትሄ መነሻ ይሆናል ነው ያሉት።