የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች እና የኦሞ ጊቤ ቤዚን የጎርፍ ተጋላጭነት ቅነሳ የቅድመ ጥናት ሪፖርት ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች እና የኦሞ ጊቤ ቤዚን የጎርፍ ተጋላጭነት ቅነሳ የቅድመ ጥናት ሪፖርት ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው። የካቲት 19/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች እና የኦሞ ጊቤ ቤዚን የጎርፍ ተጋላጭነት ቅነሳ የቅድመ ጥናት ሪፖርት ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።   የውይይት መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከዚህ ቀደም የአዋሽ ቤዚን የጎርፍ ተጋላጭነት ቅነሳ ቅድመ ጥናት ሪፖርት ላይ ውይይት መደረጉን አስታውሰው፤ ጥናቱ የህብረተሰቡን የጎርፍ ተጋላጭነት ለመቀነስ በማን፣ ምንና መቼ ይተገበራል የሚለውንም የሚመልስና በሙያዊ ስነምግባር ሊተገበር የሚገባ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።   የጎርፍ ክስተትን ለመቀነስ በጥናት ዲዛይን በማድረግ እንዴት ማቀድና መተግበር እንደሚገባ የሚያመላክት ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ቤዚኑን የሚጋሩ ክልሎች፣ ወረዳዎችና የትምህርት ተቋማት የሚሰጡት ሃሳብና አስተያየትም ለግብዓትነት ወሳኝ ነው ብለዋል። ክቡር ሚኒስትሩ ለሰነዱ ዝግጅት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።   በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ተቋሙ የተቋቋመበት ዓላማ ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ከሚሰሩ ስራዎች መካከል የጎርፍ ተቃላጭነትን መቀነስ አንዱ ነው ብለዋል።   አቶ ሞቱማ አክለውም የሚቲዎሮሎጂ ትንበያዎችን በመጠቀም ጎርፍ ከመከሰቱ በፊት ሰዎችንና የእንስሳትን ህይወት ለመታደግ በጥናት የተደገፈ የአሰራር ስርዓት ሊኖር ስለሚገባ በጥናቱ የሚቀርቡ ሰነዶችን ማዳበር ይገባል ብለዋል። በመድረኩ የኦሞ ጊቤ እና የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ቤዚን የተጋላጭነት የቅድመ ጥናት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን የሲዳማ ብ/ክ/መ/የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ፣ ከከተማና መሰረተ ልማት፣ ከግብርና፣ ከመስኖና ቆላማ አካባቢ፣ ከቱሪዝምና ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።

Share this Post