ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ፣ ጥራትና በጀት ጀምሮ የመጨረስ አቅም የታየበት መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገለፀ።

ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ፣ ጥራትና በጀት ጀምሮ የመጨረስ አቅም የታየበት መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገለፀ።   ሃዋሳ:-የካቲት 18/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በጋራ በሲዳማ ክልል ዙሪያ የተሰሩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ያሉበትን ደረጃ የመስክ ምልከታ ግብረመልስ በሰጡበት ወቅት ከክልሉ ጋር በጋራ የተሰሩት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ ጥራትና በጀት ጀምሮ የመጨረስ አቅም የታየበት ነው ብለዋል።   ከጉብኝቱ በኋላ በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተወካይ የተከበሩ አቶ መስፍን ዳኜ በክልሉ ያየናቸው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ሰው ተኮርና በዕውቀት የተመራ በመሆኑ ተሞክሮው ወደሌላ ክልል ሊሰፋ ይገባል፤ የአካባቢውንም የስራ ባህል የቀየረ ነው ብለዋል።   በተቋሙና በክልሉ መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራርና የመረጃ አያያዝ ስርዓትም ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባል የተከበሩ አቶ አለሙ ጌታሁን በበኩላቸው ስራን በዕውቀት የመምራት አቅምን ያየንበትና ችግሮችን ለመፍታት የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችም ለስራው የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።   የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት የቋሚ ኮሚቴው አባል የተከበሩ አቶ አጉ ደባን ፕሮጀክቱ ታሪክ የቀየረ፣ በቁጥጥርና አስተዳደር ላይ የነበረውን የአሰራር ስርዓት መሻሻሎችን ያየንበት በመሆኑ፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተኬደበትም የሚደነቅ ነው ብለዋል።   አሁን ያለውን የስራ ተነሳሽነት በማስቀጠል ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የክልሉን የዘመናት የመጠጥ ውሃ ጥያቄን ለመፍታት የተደረገው ጥረት የሚያስመሰግን ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴው አባል የተከበሩ ዶ/ር ሃጂ ከድር ብዙ መዋዕለ ንዋይ ወጥቶበት የሚሰራው ፕሮጀክት ቀጣይነት እንዲኖረው ስነምህዳሩን መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።   የክቡር ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ኃይሉ ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ለሰጧቸው አስተያየት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አመስግነው፤ ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓታችንን አጠናክረን በማስቀጠል የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተያየቶችን እንደግብዓት ተጠቅመን መስፈንጠሪያችን ነውም ብለዋል።   በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ጋኖሬ ውሃ ለማጠጣት ያሰብነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ከሚኒስቴር መስሪያቤቱና ከምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

Share this Post