የአለታ ወንዶ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቀጣይ ሁለት ወራት አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተባለ።

የአለታ ወንዶ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቀጣይ ሁለት ወራት አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተባለ። ሀዋሳ:-የካቲት 18/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የሲዳማ ክልል የባለድርሻ አካላት ጋር በተዘዋዋሪ ፈንድ/Revolving Fund/ የሚተገበረው የአለታ ወንዶ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቀጣይ ሁለት ወራት አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተባለ።   የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሲዳማ ክልል የአለታ ወንዶ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አፈፃፀሙን በጎበኙበት ወቅት ፕሮጀክቱ በቀጣይ ከሁለት ወራት በኋላ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል። በክልሉ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ካሉባቸው ቦታዎች አንዱ አለታ ወንዶ ነው ያሉት የሲዳማ ክልል የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ም/ኃላፊ ኢ/ር ኃ/ኢየሱስ ኤልያስ ፕሮጀክቱ በመንግስት ከፍተኛ በጀት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።   ኢ/ር ሀይማኖት አበበ የሲዳማ ክልል ዲዛይንና ግንባታ ሱፐርቪዥን ኢንተርፕራይዝ አማካሪ መሃንዲስ በበኩላቸው 2 የውሃ ሶርሶች፣ 2ሺ ሜትር ኪዩብ የሚይዝ ሪዘርቫየር እና የ45 ኪ.ሜ የውስጥ ለውስጥ የመስመር ዝርጋታንና የመካኒካል ስራዎችንም ጨምሮ የሚሰራው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ71 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።   ፕሮጀክቱ ከ471 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚተገበር ሲሆን ከ310 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶችና ለሴቶች የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት ኢ/ር ሀይማኖት አፈፃፀሙ ከ80% በላይ ነውም ብለዋል። የፕሮጀክቱ ማናጀር አቶ መላኩ አለማየሁ ቀሪ ስራዎችንም በማጠናቀቅ፣ ከተባለው ጊዜ ቀድሞ ለመጨረስና ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ያለ እረፍት እየተሰራ ነው ብለዋል።   በጉብኝቱ ወቅት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመለከታቸው መካከለኛ አመራሮች፣ የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮና የከተማው ከንቲባ የተሳተፉ ሲሆን ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎችም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምሩ ገደፋ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

Share this Post