ናይል ቀጣናዊ ትብብርን የማጠናከር ግዙፍ አቅም አለው – ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2018 ( ው.ኢ.ሚ) ናይል ሀገራትን በማስተሳሰር ቀጣናዊ ትብብርን የማጠናከር ግዙፍ አቅም አለው አሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።
'የናይል ድምጽ፡ በውሃ አስተዳደር ማህበረሰቡን በተለይም ወጣቶችና ሴቶችን ማሳተፍ' በሚል መሪ ሀሳብ የናይል ተፋሰስ ትብብር ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች በደቡብ ሱዳን ጁባ ተከብሯል።
ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለናይል ተፋሰስ ዘላቂ ዋስትና የማህበረሰቡን በተለይም የወጣቶችን እና የሴቶችን አቅም በማጎልበት አሳታፊ እና ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ያስፈልጋል ብለዋል።
ናይል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያለው አቅም የንግድ ግንኙነትን ጨምሮ ቀጣናዊ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
የተፋሰሱ ከፍተኛ የመስኖ ልማት አቅም የምግብ ሉዓላዊነትን እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን አንስተው፥ በተባበረ ክንድ ተፋሰሱ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚህም በቀጣናው በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅና የጎርፍ አደጋ መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ይቻላል ብለዋል።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ጫና በተከሰተበት በአሁኑ ወቅት የግብርናውን የዝናብ ጥገኝነት በመቀነስ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚቻል አብራርተዋል።
ናይል ሀገራትን በማስተሳሰር ቀጣናዊ ትብብርን የማጠናከር ግዙፍ አቅም እንዳለው ገልጸው፥ የተጀመረውን ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ በትብብር ማዕቀፉ መሰረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸው፥ የናይል ቤዚን ኮሚሽን ወደስራ መግባቱን በአብነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እውን ያደረገችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጣናውን ለማስተሳሰር የጎላ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፋሰሱን ሀብት እየጠበቀ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በመርሐ ግብሩ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን ገልጸው፥ ከዚህ ውስጥ 18 ነጥብ 7 ቢሊየኑ በአባይ ተፋሰስ ላይ መተከሉን ገልጸዋል።
ይህም 40 በመቶ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ውሃውን መጠቀም ብቻ ሳይሆን የመንከባከብ ስራም እየሠራች መሆኑን ያሳያል ብለዋል።