የነጻና ገለልተኛና የብዝሃነትና አካታችነት ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ አምድ ላይ ስልጠና ተሰጠ።

የነጻና ገለልተኛና የብዝሃነትና አካታችነት ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ አምድ ላይ ስልጠና ተሰጠ። ጥር 29/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የነጻና ገለልተኛና የብዝሃነትና አካታችነት ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ አምድ ላይ ለዘርፉ አመራሮችና ሰራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል።   የስልጠና መድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ በለፉት ስድስት ወራት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ውጤታማ ለማድረግ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሰራዎች መሠራታቸውን ገልጸው በሀገራችን የሲቪል ሰርቪስ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምእራፍ ለመጀመር በታለመው መጠነ ሰፊ የሪፎርም ጉዞ ላይ በመወያየት ግንዛቤ ለመያዝ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።   ሪፎርሙ የቆዩ አሰራሮችን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ ሀይሎችና የአሰራር ስርዓቶች መሠረት ዳግም በጽኑ አለት ላይ የምንገነባበት ታሪካዊ ሂደት ነው ብለዋል። የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ፍኖተ ካርታ በዘጠኝ ጽኑ አምዶች ላይ የተገነባ ነው ያሉት አቶ ኦልቀባ እነዚህ አምዶች የተቋማችን ህልውና የሚያረጋግጡ ምሰሶዎች በመሆናቸው ከአምዶቹም መካከል ቁልፍ በሆኑት በነጻና ገለልተኛና ብዝሃነትና አካታችነት ላይ ያተኮረ ስልጠና አዘጋጅተናል ብለዋል።   ነጻና ገለልተኛ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግየህዝብን አመኔታ ከማረጋገጥ ባለፈ ተቋማት የሁሉም ዜጎች አስተማማኝ መጠለያ መሆናቸውን ለማረጋገጥም እንደሚያስችል ነው አቶ ኦልቀባ የገለጹት። ብዝሃነትና አካታችነትን የተቋማችን ጥንካሬ ፣ የውበት ምንጭ እንዲሁም ጸጋና አቅም መሆኑን በመገንዘብ ስብጥሩን ይበልጥ ፍትሃዊና አካታች ለማድረግ በተለይም ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት ብሎም የወጣቱን አቅም ከሙያ እና ተሞክሮ ጋር በማቀናጀት ተቋማችንን ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።   ብዝሃነትን ያላከበረና አካታችነትን ያላረጋገጠ ተቋም ግማሽ አካሉ ሽባ እንደሆነ ሰው ነው ያሉት አቶ ኦልቀባ ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን አገራዊ ለውጡን ማፋጠን የውዴታ ግዴታችን ነውም ብለዋል። ስልጠናው ግንዛቤ ማስጨበጫ ብቻ ሳይሆን ለሙያችንና ለህሊናችን ታማኝ ልንሆን ፣ለሁሉም ዜጋ ያለአድሎና ገለልተኝነት አገልግሎት ልንሰጥ፣ ብዝሃነት ውስጥ ያለውን ውበትና ጥንካሬ አውጥተን ለተቋማችን እድገት ልንጠቀም ቃል የምንገባበት የቃል ኪዳን ማደሻና የለውጥ ሀይል መፍጠሪያች ነውም ብለዋል።   ይህ ሪፎርም በሚገባ ተግባራዊ ሆኖ የዜጎችን ህይወት እንዲቀይር ሰራተኛውና አመራሩ ቀዳሚና ወሳኝ ሚና መጫዎት እንዳለበት አቶ ኦልቀባ አጽንኦት ሰጥተዋል። የኛ ቁርጠኝነት የተቋማችን ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን ነገ ይወስናል ያሉት አቶ ኦልቀባ ብዝሃነትንና አካታችነትን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን ስንሰራ ተቋምን ከመቀየር አልፈን አገርን የሚቀይር ውጤት በተጨባጭ የምናመጣበትና እንደችግር ስናነሳቸው የነበሩ ጉዳዮችን ከመሠረቱ መፍታት የሚቻልበት እድል ይፈጥራል ብለዋል።   በስልጠናው ንቁ ተሳትፎ እና ሀሳብን በነጻነት የማንሸራሸር መብት የተጠበቀ መሆኑንና ከስልጠናው በኋላም የተሻለ አመለካከት፣ የላቀ ሙያዊ ስነምግባርና አዲስ የስራ ወኔ እና ተነሳሽነት እንደሚጨምር አቶ ኦልቀባ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በስልጠናው የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አመራሮችና ሰራተኞች እየተሳተፉ ሲሆን የቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና አመራሮች በዙም ሚቲግ እየተሳተፉ ሲሆን በውይይቱ በርካታ ሀሳቦች ፣ ጥያቄዎችና አስተያየቶች እየተንጸባረቁ ነው።

Share this Post