የኢትዮጵያ ጀርመን ኢነርጂ ትብብር አውደ ጥናት መድረክ ተካሄደ፡፡
ጥር 28/2018ዓ.ም/ው.ኢ.ሚ/የኢትዮጵያ ጀርመን ኢነርጂ ትብብር አውደ ጥናት መድረክ /Ethiopian German Energy Cooperation work shop/በ International livestock research institute/ILRI/ ቅጥር ግቢ ተካሄደ፡፡
አቶ ካሌብ ታደሰ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ሃብት ጥናት መሪ ስራ አስፈጻሚ የመርሃግብሩን ይዘት በተመለከተ እንዳስገነዘቡት ኢትዮጵያ ሃገራችን ታዳሽ ኢነርጂን አስመልክቶ እምቅ ሃብት እንዳላትና ይህንን እምቅ ሃብት ለልማቱ በሚያመች ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የአረንጓዴ ሃይድሮጂ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ የሚያስችል አውደ ጥናት የሚቀርብበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ምቹ የሆነች ሃገር ስትሆን ያለንን የውሃ ሀብት በመጠቀም ይህንን አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ከነፋስ፣ከጸሃይ ሃይል እና ከመሳሰሉት ታዳሽ ኢነርጂዎች መካከል የትኛውን ተቀዳሚ አድርገን ለልማት ብናውል ውጤታማ መሆን እንደምንችልና በኢኮኖሚም ረገድ ምቹ የስራ ዕድል የሚፈጥረውን ቴክኖሎጂ አስቀድሞ ለመተግበር በዚህ አውደ ጥናት የሚደረገው ውይይት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዚሁ አውደ ጥናት በውስጥና በውጪ ሃገር በዘርፉ የተሰማሩ አማካሪዎችን በቅጥር ያሳተፈ ሲሆን ውይይቱ በቀጥታ የበይነ መረብ የተግባቦት ልውውጥ ተካሂዷል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ብሄራዊ የአረንጓዴ ሃይድሮሎጂን ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ተግባር የገባ ሲሆን ለዚህ ቴክኖሎጂ ማስተግበሪያ የሚሆን ሃብት ለማፈላለግ እንዲቻልም በአውደ ጥናቱ ላይ የተነሱት ሃሳቦችና አስተያየቶች እገዛ እንደሚያደርጉ ከውይይቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይህ የአረንጓዴ ሃይድሮጂ ቴክኖሎጂ ከውጪ የሚገቡ ለበካይ ጋዝ የሚያጋልጡ እንደነዳጅ፣ኬሚካልና ማዳበሪያ ያሉትን የኢነርጂ ምንጮች በማደስ አካባቢን የሚበክለውን ጋዝ በእጅጉ የሚቀርፍ፣አፈር ለምነቱን እንዲጠብቅና ምርታማነቱን ለማሳደግ የለሚያስችልና በተለይም መንግስት የያዘውን የአረንጓዴ ልማት እቅድ ለማሳለጥ ስለሚያስችል ፋይዳው የጎላ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
መድረኩ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በጀርመን የልማት አጋርነት/GIZ/በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች፣የዩኒቨርሲቲ ምሁራኖች፣የጀርመን የልማት አጋር አስተግባሪዎች፣እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትና በቴክኖሎጂው ዙሪያም በርካታ ትንታኔዎች የቀረቡበት በመሆኑ በኢነርጂው ዘርፍ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሚሰሩ ስራዎች ሰፊ ግብዓት ተገኝቶበታል፡፡