ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በሐይደሮሎጂና ተፋሰስ መረጃ አስተዳደር መሪ ስራ አሰፈፃሚ እየተዘጋጁ ያሉ ሰነዶችን ገመገሙ፡፡

ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በሐይደሮሎጂና ተፋሰስ መረጃ አስተዳደር መሪ ስራ አሰፈፃሚ እየተዘጋጁ ያሉ ሰነዶችን ገመገሙ፡፡ አዳማ : ጥር /2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስተሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞተማ መቃሳ በሐይደሮሎጂና ተፋሰስ መረጃ አስተዳደር መሪ ስራ አሰፈፃሚ እየተዘጋጁ ያሉ ሰነዶችን ገምግመዋል።   ሰነዶቹ ጥራት ያለው የሐይድሮሎጂ መረጃን ለመሰብሰብ፣ የጣቢያዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ የሐይድሮሎጂ ተግባራትን በተገቢው መንገድ ለመምራትና ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ገልጸዋል። በዝግጅቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ባለሙያዎች ያመሠገኑት ክቡር አቶ ሞቱማ የሰነዶቹን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሚፈለገው ጊዜና ጥራት ተዘጋጅተው ወደ ስራ የሚገባበት ሁኔታ እንዲያፋጠን እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አካል እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡   ሰነዶችን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከሶስቱ ተፋሰስ አስተዳደር ጽ/ቤቶችና ከተፋሰስ አስተዳደር ቅ/ፅ/ቤቶች የተውጣጡ ባለሞያዎች እያዘጋጁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። የሚዘጋጁት ሰነጆችም የውሃ ሀብት መረጃ አያያዝና ማጋራት መመሪያ (water resource information management and sharing directives)፣ ብሄራዊ የሐይድሮሎጂ ጣቢያ ደረጃ (National hydrological station standard)፣ ብሄራዊ የሐይድሮሎጂ የመስክ ኦፕሬሽን መመሪያ (National Hydrological operational manual )፣ ብሄራዊ የሐይድሮሎጂ ትግበራ መመሪያ ሰነድ (national Hydrological operation guideline) መሆናቸው ተጠቅሷል።   የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ አስተዳደር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ለገሰ ሰነዶችን እያዘጋጁ ያሉትን ባለሙያዎች አመስግነው ሰነዶችቹን በማጠናቀቅ የተፋሰስ አስተዳደር ጽ/ቤቶች በተፋሰስ ደረጃ፣ የተፋሰስ ቅ/ጽ/ቤቶችም በንኡስ ተፋሰስ ደረጃ ወደ ትግበራ ማስገባት እና መጠቀም ተቋማቱ የተቋቋሙበት ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል። ለትግበራው የሁሉም ውሃ አልሚና ተጠቃሚ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ኃላፊው አክለው ገልጸዋል፡፡

Share this Post