የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ችግር ፈቺ ሊሆኑ ይገባል ተባለ።

የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ችግር ፈቺ ሊሆኑ ይገባል ተባለ።   ጥር 06/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት (BaSRINET) በአዋሽ ቤዚን ያንጉዲ ካችመንት፣ በዋቢሸበሌ ቤዚን ኦሮሚያ ክልል ባቢሌ ወረዳ ኢፋዴን ካችመንት እና በሶማሌ ክልል ዋቢ ሸበሌ ዞን አሎኢገርሲ ካችመንት ላይ ለሚተገበረው የተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅት ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና የማጠቃለያ መርሃግብር ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ችግር ፈቺ ሊሆኑ ይገባል ተባለ። በማጠቃለያ መርሃግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ችግር ፈቺ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።   በፕሮጀክት አስተባባሪነት፣ በሚ/መ/ቤቱ ዴስክ፣ በክልል፣ በወረዳ፣ በቤዚን ፅ/ቤትና በየካችመንቱ ላይ ያላችሁ ባለሞያዎች ከዚህ በኋላ ቴክኒካል መሪዎች ስለሆናችሁ ለቤዚኖቹም ሆነ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አማካሪ ናችሁ ያሉት አቶ ደበበ የፕሮጀክቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለን አጭር ጊዜ በተቀናጀ መንገድ የተተገበረ የተፋሰስ ልማት ሽፋን የሚለውን ቁልፍ አፈፃፀም አመላካች (KPI) ላይ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን ብለዋል። አቶ ደበበ አክለውም እንደ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ብሔራዊ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም (NIWRM) እስከታችኛው መዋቅር በመውረድ ለሚሰጠው ድጋፍ አመስግነው፤ ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት በክልልና በወረዳ ያሉ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችም እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።   የBaSRINET ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ በበኩላቸው በየቤዚኑ የካችመንት ማናጅመንት ፕላን ለማዘጋጀት በሁኔታ ግምገማ (Situational Assessment) የተለዩ ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት ድራፍት በማዘጋጀት በቡድን ልምምድ የተደረገ ሲሆን በቡድን ስራው ላይ በተሰጠው አስተያየት ለቀጣይ ሶስት አመታት ዶክመንት ሆኖ የሚያገለግል ዕቅድ ይዘጋጃል ብለዋል።   በካችመንት ደረጃ ችግሮችን በመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መቼና እንዴት እንደሚተገበር የሚያመላክት ዕቅድ ለማዘጋጀት ያለመ ስልጠና ነው ያሉት አቶ ሞላ በቀጣይ በየንዑስ ተፋሰሱ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሊተገበር የሚችልና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረክ የሚያስችል ማዕቀፍ/framework ይቀመጣል ብለዋል።   በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ትምህርት ክፍል የአዋሽ ቤዚን የምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሰኢድ አያሌው በታችኛው አዋሽ ቤዚን ላይ ለሚሰሩ ስራዎች በምርምር ለመደገፍ መረጃ ከማደራጀት ጀምሮ ውጤታማ ስራ ለመስራት በዩኒቨርስቲው የምርምር ማዕከል መቋቋሙን ጠቁመው፤ በያንጉዲ ካችመንት ላይ ለሚሰራውም ስራ ዕቅድ በማዘጋጀት እንዴት ወደመሬት ማውረድና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል የሚለውን እንድናይ ያደረገ ስልጠና በመሆኑ ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነትም እገዛ እናደርጋለን ብለዋል።   በዋቢሸበሌ ቤዚን የመሰረተ ልማት መሀንዲስና የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን መርኪና በካችመንት የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት፣ ሊተገበር የሚችልና ካችመንትን መሰረት ያደረገ ዕቅድ ለማቀድ ጥሩ ግብዓት እንዳገኙ ገልፀው፤ በቀጣይ በተመረጠው ካችመንት ላይ አሳታፊ የሆነና ሊተገበር የሚችል ዕቅድ አቅደን ለብሔራዊ ቲም እናቀርባለን ብለዋል።

Share this Post