የውሃ ጥናትና ዲዛይን እንዲሁም የፕሮጀክቶችን ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ከሚደግፉ አማካሪ ድርጅቶች ጋር ውል ተፈረመ።

የውሃ ጥናትና ዲዛይን እንዲሁም የፕሮጀክቶችን ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ከሚደግፉ አማካሪ ድርጅቶች ጋር ውል ተፈረመ። ጥር 6/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የውሃ ጥናትና ዲዛይን ስራዎችን ከሚያከናውን እና የፕሮጀክቶችን ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ከሚደግፉ አማካሪ ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት አድርገዋል።   የውል ስምምነቱን የፈረሙት ክቡር አምባሳደሩ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት 110 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በ55 ወረዳዎች ለመገንባት በታቀደው መሰረት እስካሁን የ50 ፕሮጀክቶች አማካሪ ቅጥር መፈጸሙን ገልጸዋል። በዛሬው እለትም በጋምቤላ ክልል ለሚገነቡ 4 ፕሮጀክቶች የጥናት፣ ዲዛይን እና የግንባታ ክትትል ስራዎችን ለማከናወን ከሬድዋን ሀይድሮሎጂ ሶሉሽን አማካሪ ድርጅት ጋር በ53, 171, 674.52 ብር በሚሆን ወጭ የውል ስምምነት ተደርጓል ብለዋል።   ድርጅቱ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በርካታ የማማከር ስራዎችን የሰራ መሆኑን የገለጹት ክቡር አምባሳደሩ ያለውን ልምድ በመጠቀም በተቀመጠው የ12 ወር የጊዜ ገደብ ፕሮጀክቱን በጥራት በማከናወን ለአገልግሎት እንዲበቃ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል። አካባቢው ውሃ ገብ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ለቁፋሮ የማያመቹ አንዳንድ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚገመት ሲሆን ድርጅቱ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ የዝናብ ወቅት ከመድረሱ በፊት ወደ ግንባታ ስራ መገባት እንዳለበት ክቡር አምባሳደሩ አጽንእት ሰጥተዋል።   ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተገንብተው የተጠናቀቁ እና የሚገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ 55 የፕሮጀክት ወረዳዎችን የሚደግፉ 12 አማካሪ ድርጅቶች መረጣ ተከናውኖ ከአሁን በፊት ከ8 አማካሪ ድርጅቶች ጋር ውል የተገባ መሆኑን የገለጹት ክቡር አምባሳደሩ በዛሬው እለትም ከ4 አማካሪ ድርጅቶች ጋር በ90,318,411.00 ብር በ18 ወራት የሚጠናቀቅ የውል ስምምነት ተፈርሟል ብለዋል።   ስራው ጥንቃቄን የሚፈልግ በመሆኑ የውሃ ተቋማትን የአሰራርና የጥገና ስርዓት ማጠናከር፣ በአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያዎች፣ በውሃ ጥራት እና የውሃ ኮሚቴዎች ያላቸውን ሚናና ኃላፊነት በግልጽ ለመለየትና ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠር፣ ውጤታማ የውሃ ታሪፍ ተመን ስርዓትን መተግበር እንዲሁም የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ ውል ከወሰዱ አራቱ ድርጅቶች የሚጠበቅ መሆኑንም ክቡር አምባሳደሩ ገልጸዋል።   በአጠቃላይ ዛሬ የተወሰደው ውል በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት በአለም ባንክ ድጋፍ እንደ ሀገር በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በድንበር አካባቢዎች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አካል ሲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ለስራው ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አክለው ገልጸዋል። የሬድዋን ሀይድሮሎጂ ሶሉሽንስ አማካሪ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ሬድዋን ኑማር በገቡት ውል መሰረት ስራውን በታቀደው ጊዜ በጥራት እንደሚያከናውኑ ቃል ገብተዋል።   የፕሮጀክቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ወረዳዎችን ለመደገፍ ውል የወሰዱት ፒቲ የውሃ አቅርቦት ሳኒቴሽንና ሀይጅን የማማከር አገልግሎት፣ ኤዲል የውሃ ስራዎች ማማከር፣ ላይቭ ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት እና ኪምኤፋሲ ውሃ ስራዎች የማማከር አገልግሎት በተወካያቸው የፒቲ የውሃ አቅርቦት ሳኒቴሽንና ሀይጅን የማማከር አገልግሎት ሰራ አሰኪያጅ በሆኑት አቶ ጳውሎስ ታምሬ አማካኝነት ሀላፊነታቸውን በሚገባ በመወጣት የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

Share this Post