ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ያለው ለገጣፎ ለገዳዲ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጎበኘ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ መስኖ ቆላማ አካባቢ እና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የለገጣፎ ለገዳዲ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ያለበትን ሁኔታ ጎበኙ።
ህዳር 12/2018ዓም(ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃ ልማት ፈንድ እያስገነባቸው ከሚገኙት የመካከለኛ ከተሞች መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እና ከ5000ሜትር ኩዩብ ውሃ የማጠራቀም አቅም ያለውን የለገጣፎ ለገዳዲ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ያስጎበኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች ፕሮጀክቶቹ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ተሰርተው ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትል ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
በተያያዘም የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዶጊሶ ጎና ፕሮጀክቱ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለና ከ250ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው ለፕሮጀክቱ መሳካት ከፌዴራል ፣ከክልልና ከከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከ5000 ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ ማጠራቀም የሚችልና ሶስት ሪዘርቫየር ያለው ሲሆን በዋገሬት ኮንስትራክሽን ግንባታው የሚካሄድ ሲሆን የማማከር ስራውን በከተማ ማሞ አማካሪ ኢንጅነሪንግ በጋራ እየተተገበረ ነው።
የውሃ መስኖ ቆላማ አካባቢ እና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አወቀ አምዝዬ ተቋሙ ጥሩ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸው በፕሮጀክቶቹ በአካባቢዎች የአካባቢ ጥበቃ እና ደህንነት ላይም የሚፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው በጉብኝት ወቅት ያገኙትን ጉድለትና ጥንካሬ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታ ማእረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ለሆኑት አቶ ሞቱማ መቃሳ ያቀረቡ ሲሆን ክቡር አቶ ሞቱማ ፕሮጀክቶቹን በተመለከተ ለተሰጠው ገንቢ ሀሳብ አመስግነው በተለይ በፍሳሽ ዙሪያ ከተሞች ላይ እንቅስቃሴ ቢኖርም አሁንም ብዙ ይቀራል በተለይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ፣ የግንባታ አካባቢን ደህንነት እና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በትላንትናው እለትም በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ እየተገነቡ ያሉትን ሁለት የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀከቶች ጎብኝቷል።