ወደ ሪፎርም መግባት ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር መሆኑ ተገለጸ።

ወደ ሪፎርም መግባት ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር መሆኑ ተገለጸ። ህዳር 11/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ቴክኖሎጂ እየዘመነ እና የህዝብ ጥያቄ እየጨመረ መምጣቱ ብሎም አለም ከደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ወደ ሪፎርም መግባት ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው ሲሉ አቶ ማሙሻ ሀይሉ ገለጹ።   በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰራተኞችን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀውን የውይይት መድረክ የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ሀይሉ ቴክኖሎጂ እየዘመነ እና የህዝብ ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ብሎም አለም ከደረሰበት ደረጃ በመድረስ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወደ ሪፎርም መግባት ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ሀገር በሁለተኛው ዙር ወደ ሪፎርም ከገቡ ተቋማት አንዱ መሆኑን የገለጹት አቶ ማሙሻ ሪፎርሙን በውጤታማነት ለመፈጸም በየደረጃው አብይ ፣ ቴክኒካል እና ንኡሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ተግባር ተገብቶ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።   አጠቃላይ ሪፎርሙን አስመልክቶ የሚቀርቡ ዶክመንቶችን በጥሞና በመከታተል ግብዓት የሚሆኑ ሀሳብ አስተያየቶችን መስጠት እንደሚገባም አቶ ማሙሻ አሳስበዋል። ሪፎርሙን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ዶክመንት ያቀረቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ እንደ ሀገር ወደ ሪፎርም ሳይገባ በፊት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ዓመታት ለሰራተኞች ምቹ የስራ ቦታና አካባቢ ከመፍጠር አኳያ በርካታ ጠንካራ ስራዎችን እንደሰራ ገልጸዋል።   አቶ ኦልቀባ ከአለም አቀፋዊ አውድ የሚወሰዱ ትምህርቶችን ፣የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ታሪካዊ ዳራ፣ ከአገራዊ አውድ የሚወሰዱ ትምህርቶች፣ ሲቪል ሰርቪሱ ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ፣ የፓሊሲው ዋና ዋና ጉዳዮች፣ ለፖሊሲው ዝግጅት መነሻ የሆኑ ገፊ ምክንያቶችን ፣ ከሪፎርሙ አምዶች አንጻር መከናወን የሚገባቸውን ዋና ዋና ተግባራትን እና የፖሊሲውን ቁልፍ የውጤት መስኮች ለውይይት በሚመች መልኩ በዝርዝር አቅርበዋል። የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ እቅድ አፈጻጸምን ደግሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስትራቴጅክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ አለሙ መንገሻ አቅርበዋል።   የዝግጅት ምዕራፉን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ወደ ሚቀጥለው የትግበራ ፣ የማጽናትና የፈጠራ ምእራፍ ለመሸጋገር ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው ሰራተኛ ድረስ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቶ አለሙ ገልጸዋል። እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም በየአምዱ በርካታ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ አለሙ ሰነዱን ለማዳበር የሚያስችሉ ግብዓቶች ከአመራሩም ከሰራተኛውም ይጠበቃል ብለዋል። የቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት ሰራተኞችም በዙም ( በኦን ላይን) ውይይቱን እየተካፈሉ ይገኛሉ።

Share this Post