የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድጅታል አሰራር ስርዓቱ የተለየ ተነሻሽነት ፈጥሯል ሲሉ የናይጄሪያ ቡድን አባላት ተናገሩ።
ህዳር 11/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድጅታል አሰራር ስርዓቱ የተለየ ተነሻሽነት ፈጥሯል ሲሉ ከናይጄሪያ ከተለያዩ ሚኒስቴር መ/ቤት የተውጣጡ ባለሞያዎች ተናገሩ።
ባለሞያዎቹ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የመጡ ሲሆን በነበረው ውይይት በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እና በኢነርጂ ልማት ዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎች ዙሪያ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
የልምድ ልውውጡን መድረክ የመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ኃይሉ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው፤ የሚኒስቴር መስሪያቤቱን አደረጃጀት፣ ተግባርና ኃላፊነትን ገለፃ አድርገዋል።
በየተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ለባለሞያዎቹ የተቀናጀ የውሃ ሀብት የተፋሰስ ክትትል ስትራቴጂ፣ የተፋሰስ እቅድና አተገባበር እንዲሁም በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሚስተዋሉትን ተግዳሮቶች ላይ ገለፃ አድርገው፤ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ተግባራዊነት ላይም በትኩረት እየተሰራበት መሆኑንም አብራርተዋል።
የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምሩ ገደፋ በተቋሙ የሚከናወኑ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ዙሪያ ያለውን ተሞክሮ ያጋሩ ሲሆን በዋን ዋሽ ብሔራዊ ፕሮግራም አማካኝነት ወደአንድ ቋት በሚገባ የገንዘብ ድጋፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ተግበራዊ ይደረጋል ብለዋል።
ከናይጄሪያ የሳህል ኮንሰልታንሲ ሲኒየር አናሊስ ሚስተር ዴቪድ ኦግዳን በተቋሙ ስለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ኢትዮጵያ ሀገራዊ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን እያሳደገች መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አዳማ ቅርንጫፍን መጎብኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዘመናዊ መንገድ ለማየት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ ያሉት ሚስተር ዴቪድ በዲጂታል የአሰራር ስርዓት ላይ የተለየ ተነሳሽነት ይፈጥራል፤ ከተቋሙ ስራ አስፈፃሚዎች የቀረበልን ገለፃ ሙሉ በሙሉ ወደየመጣንበት ተቋም ወስደን ለመተግበር ብዙ ትምህርት አግኝተናልም ብለዋል፡፡