ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተወያዩ።

ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተወያዩ። ህዳር 11/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በቅንጅት ከመጡት ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች (Mohammed Binzayid Foundation for Humanity, Gates Foundation, Children Investment Fund Foundation and Carter Centre) ጋር ተወያዩ።   ክቡር አምባሳደር በውይይቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ግንባታ እና ዘለቄታዊ አገልግሎትን አስመልክቶ ከጤና፣ ከትምህርትና ከገንዘብ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ገልፀው፤ በአሀዳዊ ዋሽ ብሔራዊ ፕሮግራም ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ሥራዎች ለማኅበረሰቡ ከማቅረብ በዘለለ በትምህርት ቤትና በጤና ተቋማት ጭምር ከለጋሽ ድርጅቶች እና ከመንግስት መደበኛ ቋት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ መሆኑን አብራርተዋል።   ክቡር አምባሳደር አክለውም የዋን ዋሽ ብሔራዊ ፕሮግራም የ2ኛው ማጠቃለያ ምዕራፍ ጥሩ አፍጻጸም ላይ እንዳለ ጥቁመው፣ በጋምቤላና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተከስቶ የቆየው በሽታ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። ከለጋሽ ድርጅቶች በሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ በአንድ ዕቅድ፣ በአንድ በጀትና በአንድ ሪፖርት የሚመራ በከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የሚመራ የላዕላይ እና ቴክኒካል ኮሚቴ እንዳለውና ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ጥሩ ተሞክሮ መሆን እንደተቻለም ገልፀዋል ።   የክቡር ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ አበራ እንዳሻው ከቡድኑ ለተነሱ ጥያቄዎች ወረዳዎች የሚመረጡበት አግባብ አንደኛው መስፈርት ለበሽታ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ቅድሚያ በመስጠት መሆኑን አብራርተው፤ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከዚህ ቀደምም ከችልድረን ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን /Children Investment Fund Foundation/CIFF/ ጋር በጋራ እየተሰራ ስላው ፕሮጀክት መልካም ተሞክሮ በማንሳት በመንግስት ደረጃም ያለውን የቅንጅታዊ አሰራር ማብራሪያ ሰጥተዋል።   ቡድኑ ከመሀመድ ቢን ዛይድ ፋውንዴሽን ፎር ሂውማኒቲ፣ ከቢልጌት ፋውንዴሽን፣ ከቺልድረን ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን እና ከካርተር ሴንተር አባላት የተውጣጡ ሲሆኑ ትኩረት የተነፈጋቸውን በሽታዎችን (Neglected Tropical Diseases) ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው እድሎች እና የሀብት ድጋፍ ለማድረግ ጥናታዊ ተልዕኮ ይዞ እንደመጣ ገልጾአል፡፡ ቡድኑ በነበረው የሦስት ቀናት ቆይታ የመስክ ጉብኝትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከገንዘብ እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር ውይይት እንደነበራቸውም ከመድረኩ መረዳት ተችሏል።

Share this Post