ለሁለንተናዊ ጤና ውሃና የውሃ አስተዳደር ሚና ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ።

ለሁለንተናዊ ጤና ውሃና የውሃ አስተዳደር ሚና ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ። ህዳር 10/2018 ዓ.ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አሁንን መከላከል ፣የወደፊትን ደህንነት መጠበቅ!በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ያለውን የዓለም የማይክሮባያል የግንዛቤ ሳምንት ከባለድርሻ ተቋማትና አካላት ጋር አክብሯል።   ከዓለም የውሃ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት /Internationale water management institute/፣ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎችም ባለድርሻ ተቋማት ጋር በትብብር በተዘጋጀው መድረክ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ለሁለንተናዊ ጤና ውሃና የውሃ አስተዳደር ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል። በውሃ ላይ ለሚራቡ ተዋህሲያን፣ለውሃ አካላትና ለአካባቢ ብክለት እና ለተያያዥ ችግሮች በሙሉ የሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት በትብብርና በቅንጅት በመስራት መፍትሄ ማምጣትና ሁለንተናዊ ጤና ማስጠበቅ እንደሚቻልም አቶ ደበበ ተናግረዋል።   ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥራቱን የጠበቀ ውሃ ለሁሉም ቤተሰብ በሚል መርህ በዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ደበበ የውሃ አካላትንና ተቋማትን የመቆጣጠርና የመረጃ አይያያዝ ስርዓት በመዘርጋት እየተተገበረ እነደሆነ ገልፀው ለውጤቱ የሁሉንም ትብብርና ቅንጅት ይሻል ብለዋል ።   ዶ/ር ዓለም ሰገድ ታምሩ በዓለም የውሃ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የዘርፉ የጥናትና ምርምር አስተባባሪ በውሃ አካላት ላይ ስለሚራቡና ለሰው የጤና ጠንቅ ስለሆኑ ተዋህስያን በአቃቂ ወንዝ ላይ ያጠኑትን የጥናት ውጤትና የብክለቱ ምክንያትና የሚያደርሰው የጤና ችግር ምን እንደሚመሰል አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል ።   በወንዞች ላይ የተለያዩ ጥቅም ላይ የማይውሉ መድሃኒቶች፣ ኬሚካሎችና የተለያየ ቆሻሻ ስለሚጣል ተዋህስያኑ መድሃኒቶችን የተላመዱ ስለሚሆኑ ሁሉም ዜጋ ድርጊቱን መቃወምና መከላከል እንዳለበት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከሌሎችም ባለድርሻ ተቋማት የመጡ ተወካዮች አሳስበው ተሳታፊዎች ተወያይተውበታል።   በመጨረሻም የዕለቱን የውይይት መድረክ ሲመሩና ሲያወያዩ የነበሩት የባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ፕ/ር ሙሉጌታ ክብረት ውሃና አንድ ጤና በሚል መነሻ ሀሳብ ባቀረቡት ጽሑፍ አንድ ጤና የሚለው ሀሳብ የሰው ጤናና የእንስሳት ጤና ተያያዥና ተመጋጋቢ መሆኑን ገልፀው ውጤቱ የስርዓተ-ምህዳር ጤናማነትንና ቀጣይነትን ይወስናል ብለዋል።

Share this Post