መጪው ትውልድ ስለሀገራችን ውሃ ሀብት ግንዛቤ እንዲኖረው ሊሰራ ይገባል ተባለ።
ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (ውኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀው 2ኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት "ውሃና ንፁህ ኢነርጂ ለዘላቂ ዕድገት" በሚል መሪ ቃል በሳይንስ ሙዚየም በተለያዩ ሁነቶች ተከበረ።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መሃሪ እንደገለፁት በክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ አነሻሽነት የተጀመረው የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ኮንፈረንስ ከአምስት አመት በፊት የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፤ በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብት ላይ ውይይት፣ መግባባትና ትብብርን ማጎልበት እንደሚገባ ገልፀዋል።
ኮንፈረንሱም በሳይንስ፣ በፖሊሲ እና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብና ግልፅ ለማድረግ፤ የምህንድስና እና የውሃ ዲፕሎማሲን ብሎም ስለ ዓለም አቀፍ የውሃ ህግ እና ዲፕሎማሲ ጥልቅ ግንዛቤን ለማዳበር ያለመ ነው ብለዋል።
በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብታችን ላይ በድርድር እና በአስተዳደር ብሔራዊ አቅምን ለመገንባት፤ መጪው ትውልድ ስለሀገራችን ውሃ ሀብት ግንዛቤ እንዲኖረው የመማማሪያ መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ሚካኤል ኮንፈረንሱ በ12 ዙር ባህር ዳር፣ ጅማ፣ አርባ ምንጭ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመግባቢያ ስምምነት ተፈራመው ወደ ስራ መገባቱንም አስታውሰው፤ በየዩኒቨርሲቲው በዙር መዘጋጀቱንም አክለዋል።
የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ኮንፍረንሱ በየተቋሙ የድርድር ዝግጁነት፣ የግንኙነት ስትራቴጂዎችን ማሻሻል እና በቴክኒክ እና በዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች መካከል የጋራ ግንዛቤን በማጎልበት መተማመንን ለመፍጠር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላትን በማስተባበር መንግስትን በዲፕሎማሲያዊ እና ቴክኒካል ጉዳዮች መደገፍ የሚችል ባለሙያዎች ለመፍጠር ያስችላል።