የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ከሶላር አቅራቢ ድርጅቶች ጋር መክረዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ከሶላር አቅራቢ ድርጅቶች ጋር መክረዋል ። መስከረም /2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ከ16 የሶላር አቅራቢ ድርጅች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። ድርጅቶቹ በጣም ገጠራማ ለሆኑ እና የሀይል ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች የሶላር ሆም ሲስተም እና ምርታማነትን በሚያሳድጉ የሶላር ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ውል ተፈራርመው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአለም ባንክ ባገኘው የ10 ሚሊየን ዶላር የብድር ድጋፍ በብርሃን ተደራሽነት ለሁሉም (ADELE) ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲደረግ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር ቀጣይነት ያለው የሶላር ስርጭት በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢ ተደራሽ እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ መሆኑንም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል። የውይይቱ ዋና ዓላማም ጅርጅቶቹ ሶላር ከማሰራጨት ጋር ተያይዞ የገጠማቸውን ችግሮች በጋራ በመወያየት የጋራ መፍትሄ ለማበጀትና በቀጣዩ የስርጭት ሂደትም የተሻለ ስራ ለመስራት ታላሚ ያደረገ ነው ሲሉ አክለዋል። ስራው ወደ መሬት ከወረደ ጊዜ ጀምሮ ከ21ሺ በላይ የሶላር ሆም ሲስተሞች 242 ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሶላር ማሽኖች ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆናቸውንም ነው ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት። ለዚህ ተግባር ማስፈጸሚያ የታቀደውን ገንዘብ ጥቅም ላይ በማዋል በቀሪ ጊዜያት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑንን የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩልም ሊፈቱና ሊታገዙ የሚገቡ ጉዳዮች በትኩረት ይሰራባቸዋል ብለዋል። የአዴሌ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲስዓለም መብራቱ ድርጅቶቹ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በገቡት ውለታ መሠረት የሶላር ስርጭቱን ሲያከናውኑ በየገጠሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኝ ከማስቻሉም ባሻገር ድርጅቶቹ የማቅረብ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል። እስካሁን በተደረገው የሶላር ስርጭት ሂደትም ከ225 ሺ በላይ የገጠር ማህበረሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸውን እና ለበርካታ ወጣቶችም የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን ነው አስተባባሪው የገለጹት። ክለውም ድርጅቶቹ ለስራቸው ማነቆ የሆኑባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከልማት ባንክና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንደሚቀረፉና በሚቀጥለው የሶላር ስርጭት ሂደት በድርጅቶች በኩል መሟላትና መስተካከል ያሉባቸውን ጉዳዮች በማስተካከል ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ የክትትልና ድጋፍ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የሶላር ስርጭት ስራው ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የገለጹት።

Share this Post