የሳኒቴሽን መሰረተ ልማቶችን በወቅቱና በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት መብቃት እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡

የሳኒቴሽን መሰረተ ልማቶችን በወቅቱና በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት መብቃት እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡ መስከረም 12/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 2ኛው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት አካል የሆነውና በ14 ከተሞች እየተገነባ ያለው የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ያለበት ደረጃ በሚገመገምበት መድረክ ላይ የሳኒቴሽን መሰረተ ልማቶችን በወቅቱና በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት መብቃት እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡ ከአንድ አመት በፊት በየከተሞቹ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በመገምገም ምን ችግሮች አሉ፤ ችግሮቹንስ በጋራ እንዴ መፍታት ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የየክልሉ የውሃ አገልግሎት ኃላፊዎች፣ አማካሪዎችና ኮንትራክተሮች በተገኙበት የተደረገው የግምገማ መድረክ ላይ ፕሮጀክቶቹ ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመሩ ቢሆንም አሁን ያሉበትን ደረጃና የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ቀርቧል፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ መድረኩን በመሩበት ወቅት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እንደሌላው ፕሮጀክት ችላ የሚባልና ጊዜ የሚሰጠው ሳይሆን ትኩረት ሰጥተን ህብረሰሰባችንን የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል። ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም በፕሮጀክቶቹ ያሉት ችግሮች ተለይተው፤ ዲዛይኑም ድጋሚ ማየት ካስፈለገ ታይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችም በዝርዝር እንዲቀርቡ አቅጣጫ ሰጥተዋል። ከመድረኩ ብዙ ተምረንበታል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ሁሉም ተቋራጭ ስራውን የራሱ በማድረግ በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎችም መሬት ላይ መታየት እንዳለባቸው፤ በሂደት ላይ ያሉም ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበው፤ በቀጣይ ብቃትን መሰረት ያደረገ ስራ በመስራት ከተሞቻችንን ፅዱ ለማድረግ ቁጭት ሊያድርብን ይገባል ብለዋል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሽንና መሠረተ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ኑረዲን መሀመድ በ14ቱ ከተሞች የተለያየ አፈፃፀም የታየ መሆኑን ገልፀው፤ በጨረታ ሂደት ላይና ኮንትራትም የፈረሙ መኖራቸውን አስታውሰው የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ፤ ጥሩ አፈፃፀማቸው በሌላቸው ፕሮጀክቶች ላይም በቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታሳቢ የተደረገ ውይይት ነው ብለዋል፡፡ አቶ ኑረዲን አክለውም ደካማ የስራ ተቋራጮች አፈፃፀም፣ በፊት በአማካሪ የተሰራው ዲዛይን እንደገና ማሻሻል በማስፈለጉ ምክንያት እንዲሁም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ፕሮክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜና በአግባቡ ሊከናወኑ አልቻሉም ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ብቻ ሲተገበር የነበረውና በአገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነው የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞች ተግባራዊ በማድረግ ከተሞቻችን ላይ የአካባቢ ንፅህና ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖረው በወቅቱና በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ እንደሀገር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

Share this Post