የሴቶችን የአመራር ብቃት ለማሳደግ የሚያግዝ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

የሴቶችን የአመራር ብቃት ለማሳደግ የሚያግዝ ስልጠና እየተሰጠ ነው። አዳማ፡ መስከረም 12/2018 ዓ.ም (ው .ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ስልጠና የሴቶችን የአመራር ብቃት ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል። ለስምንት ተከታታይ ቀናት የሚሰጠውን የስልጠና ሂደት ለመከታተል የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር ባለፉት ሁለት አመታት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞችና መካከለኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል። ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት ማብቃት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ኦልቀባ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ 50 የተቋማችን ሴት አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ያሉባቸውን ክፍተቶች በመለየት የአመራር ብቃታቸውን ለማሳደግ ብሎም ወደ አመራርነት ለማምጣት አጋዥ የሆነ ስልጠና አዘጋጅተናል ብለዋል። ተደራራቢ ሀላፊነቶች ያሉባቸውን ሴቶች ወደ አመራርነት ለማምጣት ማገዝ እንደሚያስፈልግና ሰዓታቸውን ማኔጅ አድርገው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ወሳኝነት አላቸውም ብለዋል። የተገኘውን እድልም በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የውብዳር አሚኖ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር ውል ወስዶ ወደ ተግባር ሲገባ የሰራተኞችን ክፍተት በመለየት የመፈጸም አቅምን በመገንባት ተቋማዊ ለውጥን ለማምጣት ታላሚ አድርጎ ነው ብለዋል። ስልጠናው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ብሎም ሰልጣኞቹ ያላቸውን ችሎታ አውጥተው እንዲጠቀሙና የመፈጸም አቅማቸው የተሻለ እንዲሆን ያሉባቸውን ተግዳሮቶች በመለየት የተሻለ ልምድ ያላቸውና በቅርበት ሆነው የሚያማክሯቸው የስራ ሀላፊዎችን በመመደብ ችግሮቻቸውን በዘላቂነት የሚፈቱበትን ስርዓት ያበጀ ስልጠና ነው ብለዋል። ስልጠናው ለስምንት ቀናት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች እንደሚሰጥ የገለጹት ስራ አሰፈጻሚዋ ተቋማዊ የመፈጸም አቅምን ከማሳደግ ባለፈ በእያንዳንዳችን የግል ህይወት ላይም የሚያመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል ባለመሆኑ በሚገባ ወደ ራሳችን ወስደን ልንተገብረው ይገባል ብለዋል። ለውጥ የሚጀምረው ከራስ ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚዋ ነገ የተሻልን እንድንሆን ዛሬ ላይ በማንኛውም ሁኔታ መለወጥ መቻል እንዳለብን እና አቅማችን ማሳደግ እንደምንችል ማመን ይገባል ፤ የስልጠናው አላማም ይሄ ነው ብለዋል። አለም ተለዋዋጭ እንደመሆኗ ትናንት የነበረው ዛሬ ላይ እንደነበረ እንደማናገኘውና ከጊዜው ጋር አብረን መራመድ እንድንችን በየጊዜው ራሳችንን ማብቃትና ለውጥን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብንም ብለዋል። ስልጠናው አንድ መሪ ምን አይነት ብቃት ሊኖረው እንደሚገባ ፣ ሰዓቱን እንዴት ማኔጅ አድርጎ መጠቀም እንዳለበት ፣ ግሮወዝ ማይንድ ሴትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ፣ ስራንና የግል ህይወትን እንዴት አጣጥሞ መምራት እንደሚቻል ፣ የቴክኖሎጅ አጠቃቀም እውቀታችን እንዴት ማሳደግ እንዳለብን እና ያለንን ነገር እንዴት አውጥተን መጠቀም እንደምንችል ከህይወት ልምድ ጋር ተጣምሮ እየተሰጠ ነው።

Share this Post