ለ22 ከተሞች የመረጃ አያያዝንና ልውውጥን ለማዘመንና ለማሳለጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ፡፡
መስከረም 05/2018 ዓ.ም (ውኢሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለ22 ከተሞች የውሃ አገልግሎቶችን የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማዘመንና ለማሳለጥ የሚያስችሉ በ761,990/ሰባት መቶ ስልሳ አንድ ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና/ የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገዙ የተለያዩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ድጋፍ አድርጓል ፡፡
የርክብክብ ስነስርዓቱን ያከናወኑት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ በርካታ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹ ዋና ዓላማቸው በተመረጡ 22 ከተሞች የውሃ አገልሎቶችን የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማዝመንና ለማሳለጥ በመሆኑ ተጠቃሚዎች ይህን ተገንዝበው ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል የዘርፉን ስራ ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል አላባቸው ብለዋል፡፡
አቶ ኑረዲን ሙሃመድ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሽን መሰረተ-ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹ ግዢ የተፈጸመው ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ እንደሆነና በ2ኛ የከተሞች የመጠጥ ውሃ ፕሮግራም ተግባራዊ ለሚደረግባቸው የተመረጡ 22 ከተሞች መሆኑን ገልጸው መሳሪያዎቹ ተንቀሳቃሽ ሰልክና፣ታብሌትን ጨምሮ እጅግ ውድና ዘመናዊ 10 የተለያዩ ዓይነት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች እንደሆኑ ገልጸዋል::