የሀሬ ወንዝ የመሬት አጠቃቀምን ፣ በውሃ አካላት የሚስተዋሉ ችግሮችን እና የብዝሀ ህይወት ላይ ትኩረት ያደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ለውይይት ቀረቡ።
አርባ ምንጭ : ነሀሴ26/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት አስተዳደር ጋር በጋራ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማሳለጥ የሚያስችለውን የብራት ፕሮጀክት በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች በሀሬ ወንዝ ላይ ተግባራዊ እያደረገ ነው።
የፕሮጀክቱን አተገባበር አስመልክቶ በአርባ ምንጭ ከተማ በተዘጋጀ መድረክ የሀሬ ወንዝ የመሬት አጠቃቀምን ፣ በውሃ አካላት የሚስተዋሉ ችግሮችን እና የብዝሀ ህይወትን በሚመለከት በተዘጋጁ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተሠጠው ሀላፊነት አንዱና ትኩረት የተደረገበት የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፉ መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉም ሀገራችን ያላትን የውሃ ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀም የውሃ አካላትን በተቀናጀ መልኩ የመጠበቅ እና የማስተዳደር ሀላፊነት አለበት ብለዋል።
በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለውና በርካታ ችግሮች ያሉበትን የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስን በመምራት እና በማስተዳደር ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር አካል በሆነው የብራይት ፕሮጀክት ለ5አመት ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል።
ከውሃና መሬት ሀብት አስተዳደር ጋር በጋራ የሚተገበረው የብራይት ፕሮጀክት ታላሚ የሚያደርገውም ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው አምስቱ ተፋሰሶች ላይ የመፈጸም አቅምን ለመገንባት እና የመረጃ ስርዓቱን የተሳለጠና ዘመናዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አቶ ሞቱማ ገልጸዋል።
አክለውም በጥናት ምርምር የተደገፈ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በመስራት ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃልም ብለዋል ።
በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌቴ ዘለቀ በሀገራችን ከተመረጡት 5 ተፋሰሶች አንዱ የሀሬ ተፋሰስ መሆኑን ገልፀው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚረዳ የተቀናጀ የተፋሰስ ሀብት አስተዳደር ስራዎች ለመተግበር በሀሬ ወንዝ ላይ የተሰራውን ጥናት በሌሎች ተፋሰሶች ላይም ተግባራዊ በማድረግ የተቀናጀ ውሃ ሀብትን መጠበቅ እንደሚቻል ገልጸዋል።
በተጨማሪም የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ይልቃል አንተነህ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በጣም ትንሽ በሆነ ቦታ ተግባራዊ በማድረግ ለተፋሰሱ ክፍሎች መማሪያ ሊሆን የሚችል ሞዴል ለማዘጋጀት የሀሬ ተፋሰስ ተመርጦ መጠናቱን ገልጸዋል።
የሀሬ ተፋሰስ ከፍተኛ የውሃ ሀይል ያለውና በዛውም ልክ የውሃ እጥረት የሚያጋጥመው በመሆኑ የተፋሰሱን ተጋላጭነት በመቀነስ የውሃ ሀብቱን በአግባቡ በማስተዳደር የልማት ስራዎችን ለማከናወን አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
የሀሬን ተፋሰስ እንደሞዴል መተግበሪያ ስርዓት በመጠቀም ወደ ሌሎች ቦታዎች ለማስፋት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ተፋሰሶችን በስርዓት በማስተዳደር መሬት ላይ ያሉ ሀብቶችን ማሻሻል እንደሚቻልም ገልጸዋል።
በመርሀ ግብሩ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስቴሩ አማካሪና የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ተወካይ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ከኔዘር ላንድ ኤምባሲ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ዶ/ር ቦሻ ቦምቤን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።