በኢነርጂ ሽግግር ፋይናንሲንግ እና በአየር ንብረት ኢንቨስትመንት ፕላትፎርም የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሠጠ ፡፡
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአለም አቀፍ ታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IRENA) ጋር በመተባበር በኢነርጂ ሽግግር ፋይናንሲንግ እና በአየር ንብረት ኢንቨስትመንት ፕላትፎርም ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሠጥቷል ፡፡
ነሀሴ/2017ዓም (ው.ኢ.ሚ) ፕሮግራሙ በሀገራችን ቀጣይነት ያለው የሃይል አቅርቦትን ለማሳካት ትልቅ እመርታ እንዳለውና የኃይል ሽግግር አፋጣኝ ፋይናንሲንግ (ETAF) እና የአየር ንብረት ኢንቨስትመንት ፕላትፎርም (CIP) የአቅም ግንባታ ስልጠና ለዘርፉ ሙያተኞች መሰጠቱ ወሳኝ መሆኑን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ልማት ቴክኖሎጂ ሽግግር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሀኑ ወልዱ ገልጸዋል፡፡
በሀገራችን የንጹህ ምግብ ማብሰያ ተቋማት ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ ነው ያሉት መሪ ስራ አስፈጻሚው ትብብሩ እያንዳንዱ ዜጋ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝ እና ዘላቂ የኃይል አማራጭ እንዲያገኝ የምናደርገውን ጥረት አስፈላጊነት ያጎላ ነው ብለዋል፡፡
ተደራሽነቱን ለማስፋት የፀሀይ፣ የንፋስ፣ የውሃ እና የባዮማስ የታዳሽ ሃይል ሀብቶች እምቅ አቅምን በመገንዘብ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ያለንን ታላቅ አላማ ለማሳካት በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዚህም የመንግስት ድርጅቶች፣ የልማት ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ አካላት፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የፕሮጀክት አልሚዎች በጋራ መስራታቸው አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡
በኢነርጂ ዘርፍ ለኢንቨስትመንት እና ለፈጠራ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ያለንን ሀብት ፣ እውቀት እና አቅምን በማዋሃድ የገንዘብ ድጋፍን በማግኘት የተሳካላቸው ፕሮጀክቶችን በመገንባት የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ አስፈላጊውን ማዕቀፍ መፍጠር እንችላለንም ብለዋል።
ሰልጣኞች የተገኘውን የስልጠና እድል በብቃት በመጠቀም በሚያስፈልጉት ሂደቶች እና ስልቶች በተለይ በታዳሽ ሃይል ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስትመንቶችን ለማሰባሰብ በ ETAF እና CIP ስለሚሰጡት አዳዲስ የፋይናንስ ዘዴዎች ላይ ትርጉም ያለው ተጽእኖ መፍጠር የሚያስችል እውቀት ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ከአለም አቀፍ ታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IRENA) የመጡ ባለሙያውች ስልጠናውን የሠጡ ሲሆን በተጨማሪም በውሃና ኢነርጂ በኩል ስለሚሰሩና ስለሚያስፈልጉ ድጋፎች ከኢነርጂ ዘርፍ አመራሮች ጋር በአማራጭ ኢነርጂ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ከአለም አቀፍ ታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IRENA) ጋር አጋርነት ለመመስረት እና በሃይል ሴክተሩ ላይ እድገትን የሚያሳልጡ ቅንጅቶችን ለመፍጠር እንዲሁም ለቀጣይ ዘላቂ የኃይል ምንጭ የጋራ ራዕይን ወደ ተግባር በመቀየር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ሕይወት ለማሻሻል እንደሚሰራም በውይይቱ ተገልጷል፡፡
በስልጠናው ላይ የመንግስት ድርጅቶች፣ የልማት ድርጅቶች፣ የግሉ ሴክተር አካላት፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የፕሮጀክት አልሚዎች እና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡